የደሴ ከተማን ተመራጭ የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ ነው።

0
9
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 01/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኮንፈረንስ ቱሪዝም ሰዎች ከትውልድ ቀያቸው ወይም ከሀገራቸው ውጭ ለኮንፈረንስ፣ ለሴሚናር፣ ለአውደ ጥናት፣ ለንግድ ሥብሠባዎች ወይም ለተያያዥ ዝግጅቶች የሚጓዙበት የቱሪዝም አይነት ነው።
የኮንፍረንስ ቱሪዝምን ለማስፋፋት ከሚያስፈልጉ ሃብቶች መካከል የትራንስፖርት አማራጭ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ የመሠብሠቢያ አዳራሾች፣ የገበያ ማዕከላት እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለአብነት ይጠቀሳሉ።
በአንድ ከተማ ወይም በአንድ ሀገር በሚደረግ ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች በርካታ ጥቅሞችን ይዘው ይመጣሉ። ለሆቴል እና ለትራንስፖርት የሚያወጡትን ወጭ ጨምሮ ለምግብ፣ ለመዝናኛ፣ የሀገር ውስጥ ጌጣጌጦች እና አልባሳትን ለመሸመት የሚከፍሉት ገንዘብ ቀላል አይደለም፡፡ ይህም ከዝቅተኛው የማኀበረሰብ ክፍል እስከ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዘርፍ አንቀሳቃሾች ሰፊ ዕድል ይዞ ይመጣል።
በአማራ ክልል ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭ ከኾኑ ከተሞች መካከል አንዷ ደሴ ናት። በደሴ ከተማ የጎልደን ጌት ሆቴል ሥራ አሥኪያጅ ተመስገን ፈቃዴ በከተማዋ የኮንፈረንስ ቱሪዝም እያደገ መምጣቱን ይገልጻሉ። ወደ ከተማዋ ለሚመጡ የኮንፈረንስ ተሳታፊዎች የተሻለ አገልግሎት እየሰጡ መኾኑንም ነው የተናገሩት።
አንድ እንግዳ ደኅንነቱ ተጠብቆለት ምቹ አገልግሎት እንደሚፈልግ የጠቆሙት አቶ ተመስገን ፈቃዴ ሆቴላቸው ለእንግዶች ምቹ እና ዘመናዊ የኾኑ አዳራሾች፣ የማረፊያ፣ የአልጋ እና ሌሎች አገልግሎቶችን እየሰጠ መኾኑንም አመላክተዋል።
በዘርፉ የተመረቀ የሰው ኃይል በማሟላት፣ ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት፣ የእንግዶችን እርካታ በማሳደግ ለከተማዋ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ዕድገት ኀላፊነቱን እየተወጣ መኾኑንም ተናግረዋል።
የደሴ ከተማ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ትዕግስት አበበ ከተማዋን ተመራጭ የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
ከተማዋ ቀደምት ታሪክ ያላት እና በርካታ የቱሪዝም ጸጋዎች ባለቤት ከመኾኗ በተጨማሪ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭ እየኾነች መምጣቷን ጠቁመዋል።
ይህንን አጠናክሮ ለማስቀጠልም ያሉትን ሆቴሎች ዘመናዊ እንዲኾኑ እና ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ተጨማሪ ባለ ኮከብ ሆቴሎች እንዲገነቡም እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።
የኮንፈረንስ ቱሪዝም ተሳታፊዎች ቆይታቸው እንዲራዘም እና የተሻለ እርካታ ለማምጣት የአካባቢውን ወግ፣ ባሕል፣ እሴት የሚያሳዩ ልዩ ልዩ ዝግጅቶችን ለማካተትም ታስቦ እየተሠራ ነው ብለዋል።
የወሎ አካባቢ የሚታወቅበትን የእደ ጥበብ ውጤቶችን፣ የኪነ ጥበብ ሥራዎችን፣ የባሕል አውደ ርዕዮችን፣ ተዝናኖትን የሚጨምሩ ባሕላዊ ምሽት ቤቶች እንዲስፋፉ ይደረጋል ነው ያሉት። በሆቴሎችም ተጨማሪ የባሕል ምግብ ቤቶች እንዲኖራቸውም ታቅዶ እየተሠራ እንደኾነ ነው የገለጹት።
የደሴ ከተማ የኮሪደር ልማት ከፈጠረው ዕድል፣ ካሏት ታሪካዊ እና ሰው ሠራሽ የቱሪዝም ጸጋዎች ጋር በማስተሳሰር ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል።
በአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም አገልግሎቶች ብቃት ማረጋገጥ ዳይሬክተር ደጀኔ አከለ የኮንፈረንስ ቱሪዝም አንዱ የቱሪዝም ምሰሶ መኾኑን አስረድተዋል።
የኮንፈረንስ ቱሪዝም ከሌላው የቱሪዝም አይነት ከፍ ያለ ጠቀሜታ እንዳለው አብራርተዋል። የኮንፈረንስ ቱሪዝም ተሳታፊዎች በኮንፈረንሱ ከመሳተፍ በተጨማሪ ረዘም ያለ የቆይታ ጊዜ እንዲኖራቸው እንደሚያደርግ፣ ባረፉበት መዳረሻ ሰፋ ያለ ወጭ እንዲያወጡ እንደሚያስችል፣ ደረጃቸውን የጠበቁ አገልግሎቶች ፍላጎትን እንደሚያሳድግ ጠቁመዋል። ተጨማሪ መዳረሻዎችን የመጎብኘት እድልንም እንደሚከፍት ነው ያስረዱት።
ለኮንፈረንስ ቱሪዝም መስፋፋት ደረጃቸውን የጠበቁ አዳራሾች፣ ዓለም አቀፋዊ ደረጃ ያላቸው የመኝታ ክፍሎች፣ ቀልጣፋ እና ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
ከተሞች ይህንን መሠረት አድርገው እንዲሠሩ ክልሉ አቅዶ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል። በክልሉ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከልነት አቅም ያላቸው ከተሞች መኖራቸውን ያነሱት አቶ ደጀኔ በደረጃ ተለይተው አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ድጋፍ እየተደረገ ነው ብለዋል።
የመሥተንግዶ ተቋማት ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ ፤ ባለሙያዎችንም ለማብቃት እየተሠራ ነው ብለዋል። ሆቴሎችን በኮከብ ደረጃ የመመደብ እና የሠለጠነ የሰው ኀይል እንዲኖራቸው ክትትል እና ድጋፍ እየተደረገ መኾኑንም ጠቁመዋል።
ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች እንዲገነቡ ባለሃብቶች ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ ቢሮው ድጋፍ እያደረገ መኾኑንም አብራርተዋል።
ዘጋቢ: አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here