በዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም የጎብኝዎች ማረፊያ ማዕከል እየተገነባ ነው።

0
7
ባሕር ዳር: ጥቅምት 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የዳጋ ቅዱስ እስጢፋኖስ የአባቶች አንድነት ገዳም በጣና ሐይቅ ውስጥ ከሚገኙ ገዳማት መካከል አንዱ ነው።
ገዳሙ በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአጼ ይኩኑ ዓምላክ ዘመነ መንግሥት አቡነ ሒሩተ ዓምላክ በተባሉ አባት እንደተመሠረተ የታሪክ ድርሳናቱ ያስረዳሉ፡፡ ከ800 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያላቸው ቅርሶችን ጠብቆ በመያዝ የታሪክ ማኅደር፣ የሃይማኖት ማዕከል፣ የቅርስ ባለ አደራ ኾኖ የዘለቀ ታሪካዊ ገዳም ነው፡፡
በዳጋ ቅዱስ እስጢፋኖስ የአባቶች አንድነት ገዳም የአጼ ዳዊት፣ የአጼ ዘርዓ ያዕቆብ፣ የአጼ ፋሲል፣ የአጼ ሱስንዮስ እና የሌሎችም ነገሥታት እና ቅዱሳን አጽሞች በክብር አርፈው ይገኛሉ።
አያሌ ንዋያተ ቅዱሳት፣ የነገሥታት መገልገያ ዕቃዎች፣ ካባዎች እና አክሊሎች፣ የገዳሙ መሥራች አቡነ ሒሩተ ወደ ገዳሙ የመጡበት የድንጋይ ታንኳ እና በርካታ የብራና መጻሕፍትም ይገኛሉ፡፡
ይሁን እንጂ በውስጡ ያሉት እጅግ ታሪካዊ እና ጥንታዊ ቅርሶች በጠባብ ቦታ ላይ ተደራርበው በመቀመጣቸው ምክንያት ለጎብኝዎችም አስቸጋሪ፤ ቅርሶችንም ለጉዳት የሚዳርግ ኾኖ ቆይቷል። ይህንን መነሻ በማድረግ በተባባሪ አካላት ደረጃውን የጠበቀ ሙዚዬም እየተገነባለት ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት ገዳሙን የጎብኝዎች መዳረሻ ለማድረግ ልዩ ልዩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መኾኑን የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ገልጿል።
በቢሮው የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር መልካሙ አዳም ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ በጀት በገዳሙ የጎብኝዎች ማረፊያ ማዕከል እየተገነባ መኾኑን ተናግረዋል።
ዳጋ እስጢፋኖስ በጣና ሐይቅ የሚገኙ ገዳማትን እና የቱሪስት መስህቦችን ለማስተሳሰር ወሳኝ መኾኑንም አንስተዋል። ለዚህም ደረጃውን የጠበቀ የጎብኝዎች ማረፊያ ማዕከል በማስፈለጉ በጥናት ተለይቶ ሥራው መጀመሩን ነው የገለጹት።
ገዳሙ ከባሕር ዳር እስከ ጎርጎራ ባለው የቱሪዝም መስመር ማዕከል ላይ የሚገኝ በመኾኑ ወደ ገዳሙ ለመምጣትም ይሁን እስከ ጎርጎራ ድረስ ባሉት መዳረሻዎችን ለሚጎበኙ ሁሉ ጠቀሜታው የጎላ ስለመኾኑም አብራርተዋል።
የገዳሙ አበምኔት አባ ብርሃነ ትንሣኤ ገዳሙ ከአሁን በፊት የአባቶች እና የወንዶች ምዕመናን ማረፊያ ብቻ እንደነበረ ተናግረዋል። ወደ ገዳሙ የሚመጡ ሴት ምዕመናን የማረፊያ ቦታ ባለመኖሩ ገዳሙን ጎብኝቶ ለመመለስ እንደሚቸገሩም አንስተዋል። አሁን እየተገነባ ያለው የጎብኝዎች ማረፊያ ይህንን ችግር እንደሚፈታም ገልጸዋል።
ለቅርሶች ማስቀመጫ ሰፊ ቦታ ባለመኖሩ በርካታ ቅርሶች በጠባብ፣ በጨለማ እና በአስቸጋሪ ሁኔታ ተቀምጠው እንደሚገኙ ነው የተናገሩት። እየተገነባ ያለው ሙዚዬም ቅርሶች ደኅንነታቸው ተጠብቆ እንዲቀመጡ እና ለጎብኝዎች ክፍት እንዲኾን ጠቀሜታ እንዳለውም አመላክተዋል።
በቦታ መጥበብ ምክንያት ቅርሶች ተደራርበው የሚገኙ እና ለጉዳት እየተዳረጉ መኾኑን ጠቁመው የተገነባው ሙዚየም ቅርሶች ደኅንነታቸው ተጠብቆ እንዲቀመጡ ሚናው የጎላ ነው ብለዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here