ክልሉን የሚጎበኙ የውጭ ቱሪስቶች ቁጥር እየጨመረ ነው።

0
8
ባሕር ዳር: ጥቅምት 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ክልሉን የሚጎበኙ የውጭ ቱሪስቶች ቁጥር እያደገ መምጣቱን የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ አስታውቋል።
በአማራ ክልል በርካታ የሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ የቱሪዝም መዳረሻዎች ይገኛሉ። በክልሉ ሕዝብ የሚዘወተሩ እና የጎብኝዎችን ቀልብ የሚስቡ አያሌ ቱባ የባሕል እሴቶች እና ክብረ በዓላትም በቱሪስት መስህብነት እያገለገሉ ይገኛሉ።
የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ጸጋዬ ከሀገር ውስጥ ጎብኝዎች በተጨማሪ የውጭ ቱሪስቶችን ቁጥር ለማሳደግ ቢሮው ከአስጎብኝ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየሠራ መኾኑን አብራርተዋል።
ከአሁን በፊት በስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ በጎንደር፣ በባሕር ዳር፣ በላሊበላ እና በደሴ ከተሞች የሚገኙ መዳረሻዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የውጭ ቱሪስቶች መጎብኘታቸውን ለአብነት አንስተዋል።
ቢሮው ክልሉን የሚጎበኙ ቱሪስቶች የተራዘመ የቆይታ ጊዜ እንዲኖራቸውም በየመዳረሻዎች የሚገኙ ሆቴሎችን እና የአገልግሎት ሰጭ ተቋማትን የመከታተል እና የመደገፍ ሥራዎችን እያከናወነ መኾኑንም አመላክተዋል።
በ2018 በጀት ዓመትም የተጠናከረ የግብይት እና የፕሮሞሽን ሥራዎችን በማከናወን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የውጭ ጎብኝዎች ክልሉን እንዲጎበኙት እየተሠራ መኾኑን ነው አቶ መልካሙ የገለጹት።
በመዳረሻ ስፍራዎች የቱሪዝም ምርቶችን ማሳደግ፣ እሴቶችን መጨመር እና የተሟላ የፕሮሞሽን ፓኬጆችን በመቅረጽ ወደ ሥራ መገባቱንም አመላክተዋል። ይህንን ተከትሎም የውጭ ጎብኝዎች በቡድን እና በተናጠል ወደ ክልሉ በመምጣት እየጎበኙ እንደኾነ ነው የተናገሩት።
በዛሬው ዕለትም በአማራ ክልል የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለመጎብኘት ከሩስያ የመጡ 30 አባላትን የያዘ የጎብኝዎች ቡድን ወደ ክልሉ ገብተዋል።
የልዑካን ቡድኑ አስጎብኝ የኾነው አበበ ያረጋል ይህንን ያህል ቁጥር የውጭ ጎብኝዎች በቡድን ኾነው በአንድ ጊዜ ወደ ክልሉ መምጣት የቱሪዝም ገጽታውን በመገንባት እና ለሌላው ጎብኝ መልዕክት የሚያስተላልፍ መኾኑን አመላክተዋል።
የውጭ ሀገር ቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር ያደርጋልም ብለዋል። በቀጣይ በሚደርሱበት መዳረሻ ስፍራዎችም ተገቢውን መረጃ በመስጠት እና በማስተናገድ መልካም ቆይታ እንዲኖራቸው እናደርጋለን ነው ያሉት።
ጎብኝዎች በቆይታቸው ባሕር ዳርን እና የጣና ሐይቅ ደሴቶችን ጨምሮ በክልሉ የሚገኙ ዋና ዋና መዳረሻዎችን ለማስጎብኘት በዕቅድ ስለመያዙም አቶ አበበ ጠቁመዋል።
በተደጋጋሚ ወደ ክልሉ የሚመጡ ጎብኝዎችን ተገቢውን አገልግሎት በመሥጠት ክልሉን የሚጎበኙት ጎብኝዎች ቁጥራቸው እንዲጨምር የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ ስለመኾኑም አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here