“ታሪክ የመላባት፣ ሃይማኖት የጸናባት ዑራ ኪዳነ ምሕረት”

0
56
ባሕር ዳር: ጥቅምት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎ወርቃማው እና አምሳለ ልቡ ጣና ሐይቅ በውስጡ በርካታ ደሴቶች እና ገዳማት ይገኙበታል፡፡
ጣና ሕይቅ ከያዛቸው ውብ ሥፍራዎች መካከል ደግሞ ዘጌ ባሕረ ገብ አካባቢ አንደኛው ነው። በጣና ሐይቅ የሚገኘው የዘጌ ባሕረ ገብ መሬት ባለው የተፈጥሮ ጥብቅ ደን እና በውስጡ አቅፎ በያዛቸው ታሪካዊ ገዳማት ይታወቃል፡፡
በዘጌ ከሚገኙት ገዳማት መካከል ደግሞ የሐመረ ኖኅ ዘጌ ዑራ ኪዳነ ምሕረት የደብረ ሥላሴ እና ምዕራፈ ቅዱሳን ዋሻ መድኃኒዓለም ገዳም አንዷ ናት።
‎ገዳሟ ከባሕር ዳር ከተማ በአማካይ በጀልባ የአንድ ሰዓት ጉዞ ከሄዱ በኋላ ትገኛለች። ዘጌ በየብስ ከባሕር ዳር 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ታሪካዊ ሥፍራ ናት፡፡
‎የሐመረ ኖኅ ዘጌ ዑራ ኪዳነ ምሕረት ገዳም የሙዚየም ኀላፊ እና አስጎብኝ አባ ገብረ ሥላሴ አበበ ገዳሟ በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያዊው አባት አቡነ ዮሐንስ እንደተመሠረተች ይናገራሉ።
‎የቤተ ክርስቲያኗ አሠራር ጥንታዊ መኾኑንም ተናግረዋል። ‎ቤተ ክርስቲያኗ በክብ ቅርጽ የተሠራች ናት። የገዳሟ ቅኔ ማህሌት ከሸንበቆ፣ ቅድስቱ እና መቅደሱ ከጭቃ እና ከድንጋይ የተሠራ ነው ይላሉ። በር እና መስኮቶቹ የተሠሩባቸው እንጨት እና ጥበብ ሌላው የገዳሟ ታሪካዊነት ምስክር ነው ብለዋል፡፡
‎ዑራ ኪዳነ ምሕረት የብዙ ጎብኝዎችን ቀልብ የምትስበው በመቅደሱ ዙሪያ መጽሐፍ ቅዱስን እና ትውፊትን መሠረት አድርገው በተሳሉ ድንቅ የግድግዳ ላይ ስዕሎቿ አማካኝነት እንደኾነም ገልጸውልናል፡፡
‎በቤተ ክርስቲያኗ የውስጡ ክፍል በአራቱም አቅጣጫ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮን የሚናገሩ ሥዕሎች የተመላ ነው።
‎በሰሜን በኩል ሃይማኖታዊ ተጋድሎን ያደረጉ የሰማዕታት ታሪክን የሚያትቱ ሥዕሎች ይገኛሉ፡፡ በደቡብ በኩል ደግሞ የድንግል ማርያም ስደት እና ሌሎች ተያያዥ ታሪኮችን የሚያሳዩ ስዕሎች አሉበት። በምሥራቅ በኩል የኢየሱስ ክርስቶስ የሆሳዕና ሥርዓትን እና በምዕራብ በኩል ደግሞ የኢየሱስ ክርስቶስን ከልደቱ ጀምሮ እስከ ዳግም ምጽዓት ያለውን ታሪክ ያሳያል ነው ያሉት፡፡
‎ሥዕሎች ረጅም ዓመታትን ያስቆጠሩ ቢኾንም ደማቅ ቀለማቸው እና ውበታቸው አሁንም ድረስ ጎልቶ ይታያል።
‎በገዳሙ ቅጥር ግቢ ውስጥ ገዳሙን የመሰረቱት አቡነ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያኑን ከማነጻቸው በፊት ያሠሩት ቤተ ዮሐንስ የሚባለው ቤተ ማዕድ ወይም ቤተ ምርፋቅ ይገኛል። ይህም ቅርስ ተጨማሪ ውበት እና መስህብ ነው።
በውስጡም ጠላ እና ጠጅ ይዘጋጅባቸው የነበሩ እና ከእንጨት የተሠሩ ከ600 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠሩ ሦስት ትልልቅ ጋኖች ይገኛሉ ነው ያሉን፡፡
‎በዑራ ኪዳነ ምሕረት ውስጥ በርካታ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ቅርሶች ደረጃውን በጠበቀ እና ባለ አንድ ፎቅ ሙዚየም ተሠርቶላቸው እንደሚገኙ ተናግረዋል። ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ ሙዚየሙ ተደራጅቶ ለጉብኝት ክፍት መኾኑንም የሙዚየሙ ኀላፊው ለአሚኮ ገልጸዋል፡፡
‎በሙዚየሙ ውስጥ ከ500 ያላነሱ ጥንታዊ የብራና መጻሕፍት፣ በተለያዩ ነገሥታት ለገዳሙ የተበረከቱ የነገሥታት ዘውዶች እና አልባሳት፣ መስቀሎች እና ልዩ ልዩ የመገልገያ ንዋየ ቅዱሳት እና ሌሎች ውድ ቅርሶች ተደርድረው እየተጎበኙ መኾኑንም ተናግረዋል።
‎በገዳሙ መጽሐፈ ቀለሚንጦስ፣ መጽሐፈ ሲኖዶስ፣ ዜና አይሁድ እና ዜና እስክንድር የሚባሉ በብዙ ቦታዎች የማይገኙ ሃይማኖታዊ የብራና መጻሕፍት ይገኛሉ፡፡
‎ገዳሙን ለመጎብኘት በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ቱሪስቶች የሚመጡበት ገዳም ነው፡፡ በዚህ ዓመትም ከመስከረም ወር ጀምሮ የቱሪስት ፍሰቱ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
‎ከወደቡ ወደ ቤተክርስቲያኑ ለመድረስ በተለይ በክረምት አስቸጋሪ የነበረው የእግረኛ መንገድ አሁን ላይ በክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ በመሠራቱ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል፡፡
‎ገዳሙ የሚገኘው በጣና ሐይቅ ዳር በደን በተከበበ ቦታ ነው፡፡ በውስጡ የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶች እና የግድግዳ ላይ ስዕሎቹ የቱሪስቶችን ቀልብ የሚስቡ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል፡፡
‎በክልሉ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ድጋፍ ቤተ መቅደሱ ያጋጠመውን የቅርስ ጉዳት የጥገና ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ ከወደቡ ወደ ገዳሙ የሚወስደው 1 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር መንገድ በጌጠኛ ድንጋዮች ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ ተሠርቶ ለጎብኝዎች ምቹ ተደርጓል፡፡
‎ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ላይ የጽዳት፣ እንክብካቤ እና የቁጥጥር ሥራዎች ይሠራሉ ተብሏል፡፡
‎ዘጋቢ፡- ፍሬሕይዎት አዘዘው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here