የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የቱሪዝም ፍሰት መነቃቃት እያሳየ ነው።

0
21
ባሕር ዳር: ጥቅምት 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በቱሪዝም በዓለም ከምትወደድባቸው ሥፍራዎች መካከል አንደኛው ነው። በሌሎች ዓለማት የማይገኙ ብርቅዬ እንስሳትን የያዘ እና የሚያምር የተፈጥሮ ውበትንም የታደለ ነው የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ።
ይህ አስደናቂ ውበት ያለው ሥፍራ በየትኛውም የዓለም ጫፍ የሚገኙ ጎብኝዎችን በመሳብ ይታወቃል። በውስጡ የያዛቸውን ብርቅዬ እንስሳትን እና ተፈጥሮ የለገሰችውን ውበቱን ለማየት የሚሹ ጎብኝዎች ሲመላለሱበት ኖረዋል።
ይህ ውብ ሥፍራ ለኢትዮጵያ ቱሪዝም ታላቅ አበርክቶ ሲያደርግ ኖሯል። ነገር ግን በተፈጠሩ ተደጋጋሚ ችግሮች የጎብኝዎች መዳረሻ የነበረው ሥፍራ ያለ ወትሮው ጎብኝዎችን ለመናፈቅ ተገድዶ ነበር።
የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ የሰሜኑ ጦርነት እና አሁን ላይ በአማራ ክልል ያለው ግጭት ወደ ስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ይሄዱ የነበሩ ጎብኝዎችን የቀነሱ ምክንያቶች ናቸው።
የጎብኝዎች ፍሰት በመቀነሱ ደግሞ በተለይ በሆቴል ቱሪዝም እና በአስገብኝዎች ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና ፈጥሮ ቆይቷል። በስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ባሕላዊ መጓጓዣ አቅራቢዎች፣ ጠባቂዎች፣ አስጎብኝዎች፣ የሆቴል ባለሀብቶች እና ሌሎች ተጠቃሚዎች ናቸው። ችግር ሲፈጠርና የጎብኝዎች እንቅስቃሴ ሲቀንስ ግን እነዚህ ሁሉ ተጎድተዋል።
የዋልያ አስጎብኝዎች ማኅበር ሊቀመንበር ካሳ ብርሃኔ
የዋልያ አስጎብኝ ኅብረት ሥራ ማኅበር ከተመሰረተ ከ30 ዓመታት በላይ የኾነው አንጋፋ እና በስሜን ብሔራዊ ፓርክ የመጀመሪያው አስጎብኝ ማኅበር መኾኑን ተናግረዋል፡፡
የቱሪስት ፍሰቱ መቀነስ ቱሪዝም ቀጥተኛ የገቢ ምንጫቸው ለኾኑ ሰዎች ጉዳት ማስከተሉን ጠቁመዋል።
ላለፉት አምስት ዓመታት የቱሪስት ፍሰቱ በመዳከሙ የማኅበሩ አባላት ቤተሰቦቻቸውን ለማሥተዳደር ሲሉ ከአካባቢያቸው ተሰደው በዝቅተኛ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
ሰላም ከሌለ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ማስኬድ አይቻልም ያሉት የማኅበሩ ሊቀመንበር ይህም ሀገርንም ኾነ ግለሰብን እየጎዳ ነው ብለዋል።
ቱሪዝሙን ወደ ነበረበት ለመመለስ እያንዳንዱ የማኅበሩ አባላት በከፈቱት የማኅበራዊ ድረ ገጽ በኩል መልካም ገጽታ የመገንባት ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
በደባርቅ ከተማ የቴዎድሮስ ሎጅ ሥራ አሥኪያጅ ቸርነት አንዳርጌ ሎጅው በቱሪስቶች ተወዳጅ እና ተጠቃሚ እንደነበር አንስተዋል። በስሩ ለ42 ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥሮ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
አሁን ላይ ግን የቱሪስት ፍሰቱ በጣም በመቀዛቀዙ የነበሩት ሠራተኞች በግማሽ መቀነሳቸውን ተናግረዋል፡፡
ይህም ብቻ ሳይኾን በቱሪዝሙ ዘርፍ ይገኝ የነበረውን ገቢ 98 በመቶ ማጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ አሁን በታየው አንጻረዊ ሰላም ምክንያት በጥቂቱም ቢኾን እንቅስቃሴ መታየቱን ተናግረዋል።
ቱሪዝም በባሕሪው ሰላም ይፈልጋል፤ ስለዚህ ሰላምን ለማምጣት ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የኮረና ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ በተፈጠሩ ችግሮች ምክንያት የቱሪስት እንቅስቃሴው እየቀነሰ መምጣቱን የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ተወካይ ኀላፊ ላቀው መልካሙ ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል በዓመት እስከ 30ሺህ የሚደርሱ ቱሪስቶች ብሔራዊ ፓርኩን ይጎበኙት እንደነበር አስታውሰዋል። አሁን ላይ ያለው እንቅስቃሴ ዝቅተኛ ነው ብለዋል፡፡
ቱሪዝም በባሕሪው ሰላም ይፈልጋል ያሉት ተወካይ ኀላፊው ጎብኝዎች ወደ አካባቢው ሲመጡ ደኅንነታቸው መጠበቅ አለበት ነው ያሉት።
ያም ኾኖ በ2016 ዓ.ም ከነበረው የቱሪስት ጎብኝዎች ቁጥር በአንጻራዊነት ሲታይ የ2017 ዓ.ም ጎብኝዎች ቁጥር ተሻሽሏል ብለዋል፡፡
በዚህም እስከ 4ሺህ የሚደርሱ ቱሪስቶች ፓርኩን መጎብኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ይህም ቱሪዝሙ መነቃቃት እየታየበት መኾኑን የሚያሳይ እንደኾነ ነው የተናገሩት፡፡
በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ወራት ከነበረው የተሻለ የቱሪስት ቁጥር መመዝገቡንም አብራርተዋል፡፡
በዚህ ከቀጠለ የቱሪዝም እንቅስቃሴው ወደ ነበረበት ይመለሳል የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡
አሁን የታየውን አንጻዊ ሰላም የበለጠ በማጠናከር እንደሀገር ከቱሪዝም የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ሁሉም ርብርብ ማድረግ ይገባዋል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ:- ሰናይት በየነ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here