የአጼ ምኒልክ የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤት- ኮራማሽ

0
41
ባሕር ዳር: ጥቅምት 20/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ዳግማዊ አጼ ምኒልክ በንግሥና ዘመናቸው የኢትዮጵያን የውስጥ አንድነት ለማስጠበቅ እና ከውጭ ጠላት ለመከላከል በርካታ ተጋድሎዎችን አካሂደዋል።
በመሪነት ዘመናቸው በበርካታ ቦታዎች አሻራቸውን አስቀምጠዋል። እነዚህ አሻራዎች ዛሬም ድረስ ለዓብነት እየተጠቀሱ የትውልድ ማስተማሪያ መኾናቸውን ቀጥለዋል።
የአጼ ምኒልክ የታሪክ አሻራ ካረፈባቸው ሥፍራዎች መካከል “ሳላይሽ” የሚል ስያሜ የተሰጠው የኮራማሽ የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤት አንዱ ነው።
የጦር መሳሪያ ግምጃ ቤቱ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሀገረ ማርያም ከሰም ወረዳ ይገኛል። ከባሕር ዳር 651 ኪሎ ሜትር፣ ከደብረ ብርሃን 68 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ያረፈበት ቦታ 15 ሺህ 595 ሜትር ስኩየር ይሸፍናል።
የአካባቢው ነዋሪ እና ከ40 ዓመታት በላይ በመምህርነት አገልግለው አሁን በጡረታ ላይ የሚገኙት መምህር ሰይፈ ኃይለገብርኤል የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤቱ በ189ዐ ዓ.ም እንደተመሠረተ ያስረዳሉ:: የአጼ ምኒልክ ዋነኛ የጦር ማከማቻ ኾኖ ያገለገለ ቁልፍ ቦታ መኾኑንም ነው የገለጹት።
መምህር ሰይፈ እንዳብራሩት ለጦር መሣሪያ ግምጃ ቤቱ ዋነኛ መመሥረት አጼ ምኒልክ የዓደዋን ጦርነት ድል ካደረጉ በኋላ ጠላት በቀላሉ የማይደርስበት የጦር መሣሪያ ማከማቻ ስትራቴጂካዊ ቦታ በመፈለጋቸው ነው።
“ሳላይሽ” የሚለውን ስያሜ በተመለከተ መምህር ሰይፈ እንደገለጹት ንጉሠ ነገሥቱ የሚፈልጉትን ቦታ ለማግኘት የበታች ሹማምንቶችን ሲያማክሩ በወቅቱ የቡልጋው ገዥ የነበሩት ራስ ዳርጌ ከግዛታቸው ምቹ የኾነ ቦታ እንዳለ ያሳውቋቸዋል። አጼ ምኒልክም በተሰጣቸው ጥቆማ መሠረት ቦታውን ሄደው ያዩታል።
ቦታውን ባዩ ጊዜ ተስማሚ መኾኑን ሲረዱ ከዚያ በፊት የቦታውን ጠቃሚነት ሳያዩት ቆይተው “እንዴት እስካሁን ሳላይሽ ቆየሁ” ብለው በመገረማቸው ሥፍራውን “ሳላይሽ” ብለው እንደሰየሙት አስረድተዋል:: ከዚያ ጀምሮ የቦታው ስያሜ “ሳላይሽ” እየተባለ እንደሚጠራ መምህር ሰይፈ አብራርተዋል::
የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤቱ በዘመኑ ድንቅ የቤት አሠራር ጥበብ የተቸረበት ከድንጋይ፣ ከእንጨት እና ከጭቃ በእንቁላል ቅርጽ የተሠራ እንደኾነ ነው የሚገልጹት። ይህ ድንቅ የቤት አሠራር ጥበብ እስከ ዛሬ ድረስ ሳይፈርስ እንዲቆይ አስችሎታል ነው ያሉት።
በወቅቱ ለግንባታው የተጠቀሙት ቆርቆሮ ከፈረንሳይ የመጣ መኾኑን ነው የገለጹት። በውስጡ መሣሪያው የሚቀመጥበት ራሱን የቻለ ቆጥ ተሠርቶለት ስውር መስኮቶች እንዳሉትም አስረድተዋል።
መምህር ሰይፈ እንደገለጹት ከ189ዐ ዓ.ም ጀምሮ 36 ዓመት በጦር መሣሪያ ግምጃ ቤትነት አገልግሏል። አጼ ምኒልክ ከውጭ ሀገራት የጦር መሣሪያ እና ጥይቶችን በማምጣት ያከማቹበት ነበር። በወቅቱ ሰነኒ፣ ስናድር፣ ውጅግራ የሚባሉ የጦር መሣሪያ አይነቶች እና ጥይቶች ይቀመጡበት እንደነበር ለአብነት አንስተዋል።
በ1928 ዓ.ም ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜም በግምጃ ቤቱ የነበረው የጦር መሣሪያ እና ጥይት በአቅራቢያ ወደ ሚገኘው ዋሻ መወሰዱን ነው የተናገሩት።
ቀሪውን መሣሪያ አጼ ኃይለ ሥላሴ በጣሊያን እጅ እንዳይገባ በማሰብ ለአርበኞች መዋጊያ እንዲኾን ማስደረጋቸውን መምህር ሰይፈ አስረድተዋል። ወራሪው ኃይልም ከሥፍራው ሲደርስ በግምጃ ቤቱ የጦር መሣሪያ እንዳላገኘ ገልጸዋል::
የሀገረ ማርያም ከሰም ወረዳ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ውበቴ ሀብታሙ ግምጃ ቤቱ ከተገነባ ጀምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን እየሰጠ ለዛሬው ትውልድ መድረሱን ገልጸዋል። ከ1890 ዓ.ም እስከ 1928 ዓ.ም የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤት፤ ከ1928 ዓ.ም እስከ 1933 ዓ.ም ጣሊያኖች ተጠቅመውበታል ብለዋል። ከ1933 ዓ.ም እስከ 1966 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በፖሊስ ጦር ማሠልጠኛነት አገልግሏል።
ይህ ታሪካዊ ስፍራ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በቋሚ ቅርስነት ተመዝግቦ ለጉብኝት ክፍት መኾኑን ጠቁመዋል። ቅርሱ በፊት የመፈራረስ አደጋ ገጥሞት እንደነበር አንስተዋል። ከፌዴራል ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተገኘ ድጋፍ ጥገና እንደተደረገለትም ተናግረዋል::
ታሪካዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ አልምቶ በወረዳው ከሚገኙ ሌሎች የመሥህብ ሃብቶች ጋር በማሥተሳሰር የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን ነው ያመላከቱት።
ግቢው እንክብካቤ እየተደረገለት ለጎብኝዎች ክፍት ተደርጎ ገቢ እያስገኘ መኾኑን ነው የተናገሩት። ይህንን ታሪካዊ ቅርስ እና የቱሪስት መሥህብ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኝዎች እንዲጎበኙትም ኀላፊዋ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here