እርፎ መረባ “የእናቶች የሰላም ተማጽኖ”

0
9
ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) እርፎ መረባ የሰላም፣ የእርቅ እና የበጎነት ምልጃ ነው። ባሕላዊ ሥርዓቱ ወሎ አካባቢ በስፋት ይከወናል፡፡
እርፎ መረባ የተፈጥሮም ኾነ ሰው ሠራሽ ችግሮች ሲከሰቱ ከችግሩ እንዲጠብቃቸው እናቶች ሰብሰብ ብለው ፈጣሪን የሚለምኑበት ሥርዓት ነው፡፡ እነዚህ እናቶች ዱበርቴዎች ይባላሉ። ዱበርቴ ማለት አስታራቂ ማለት ነው።
ዱበርቴ መሰሉ ስሁል የአላማጣ ነዋሪ ናቸው። ከእሳቸው በፊት እናታቸውና አያታቸው ዱበርቴዎች እንደነበሩ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
እርፎ መረባ ያለምንም የሃይማኖት እና የዘር ልዩነት አስታራቂዎች ሰብሰብ ብለው ፈጣሪን በጸሎት መጠየቂያ ባሕላዊ ሥርዓት ነው ብለዋል። ችግር ሲገጥም እና ደስታ ሲኖር በራስ ተነሳሽነት ተፈላልገው እንደሚገናኙም ገልጸዋል።
ስለ ሀገር እና ሰዎች ሰላም፣ ደኅንነት፣ አንድነት እና ፍቅር፣ ይቅር መባባል በጸሎት ፈጣሪን እንደሚለምኑ ነው የነገሩን። ሀገር የሚነጣጥል ሀሳብ በእርፎ መረባ ጊዜ የሚያንጸባርቅ ዱበርቴ ካለ ግን እንደሚገለልም ተናግረዋል።
የክዋኔ ሥርዓቱ ራሱን የቻለ አለባበስ፣ አጊያጊያጥ፣ የምግብ አዘገጃጀት እና አመጋገብ፣ የእርቅ ሥርዓት እና ቃላዊ ዜማ እንዳለውም ገልጸዋል።
ሀገር ሰላም ይሁን እርፎ መረባ-መረባ
ገዥ ከገዥ ያስማማልን እርፎ መረባ-መረባ
ጥልን ያርቅልን ወንድም እህት ነን እርፎ መረባ-መረባ
እባክህ ፈጣሪ ጸቡን አስቁምልን እርፎ መረባ-መረባ
እያሉ ከጸለዩ በኋላ ተመራርቀው እንደሚለያዩ ገልጸውልናል።
ሌላኛዋ የአላማጣ ከተማ ነዋሪ ዱበርቴ ሸዋየ ሞላ ደግሞ እናታቸው ዱበርቴ እንደነበሩ እና እርሳቸው እንደቀጠሉም ተናግረዋል። ሰው ሲጣላ እናስታርቃለን፣ ሲያገባ ትዳሩ እንዲሰምር እንጸልያለን፣ ሲሞትሞ እንጸልያለን ነው ያሉት።
ዱበርቴ ኾኖ ቅራኔ ካለ መጀመሪያ እርቅ ማውረድ እና ልብን ንጹሕ ማድረግ ይጠበቃል ነው ያሉት። ለራስ ሳይኾኑ ለሌላ አስታራቂ መኾን አይቻልምም ብለዋል። ዱበርቴ ለእርቅ ጠይቆ እምቢ የሚል ሰው እንደማይኖርም ጠቅሰዋል።
ለእርቅ ሲጠየቅ እምቢ ብሎ ችግር የሚገጥመው ሰው ቢኖር አብሮት የሚቆም አይኖርም፤ መስማማት ግድ ነው ብለዋል። አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ቀጠሮ መስጠት ግን ይኖራል ነው ያሉት።
አሁን ላይ በአማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ ችግር እንዲቀረፍም እየተገናኙ እርፎ መረባ እንደሚሉ ነግረውናል።
የሰሜን ወሎ ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ገነት ሙሉጌታ እርፎ መረባ በዘወልድ የእርቅ እና ሽምግልና ሥርዓት ውስጥ የሚካተት ባሕላዊ የእርቅ ሥርዓት እንደኾነ ተናግረዋል። በዘወልድ የተጀመረ የእርቅ ሥርዓት እርፎ መረባ እያሉ ዱበርቴዎች ያሳርጉታል ነው ያሉት።
እርፎ መረባ ቂም ይቅር፣ ችግር ይፈታ፣ ሰላም ይምጣ ብለው ዱበርቴዎች ፈጣሪን በጸሎት የሚጠይቁበት እና የሚመርቁበት ባሕል መኾኑንም ጠቅሰዋል። ሥርዓቱ በክልል ደረጃም እውቅና የተሰጠው እንደኾነ ነው የገለጹት።
ከወልድያ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመኾንም ባሕላዊ የእርቅ ሥርዓቶች ላይ የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎችን ሢሠሩ መቆየቱንም ጠቅሰዋል። እንደ ባሕል እና ቱሪዝም ግን የተሠሩ የድጋፍ እና ክትትል ሥራዎች ዝቅተኛ እንደኾነም ገልጸዋል።
የእርቅ ሥርዓቱን እውቅና ኑሮት ወደፊት ተከታታይ ሥራ እንዲሠራ ለማድረግ የባሕል ማዕከል ራያ ቆቦ ላይ እየተገነባ እንደኾነ ተናግረዋል። እርፎ መረባ እና ሌሎች ባሕላዊ የእርቅ ሥርዓቶች የሰላም አንዱ ምንጭ ስለኾኑ ሥልጠና መስጠት እንዲቻል አጋር አካላት እንዲተባበሩም ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ የባሕል እሴቶች ልማት ባለሙያ ነህምያ አቤ ባሕላዊ የእርቅና ሽምግልና ሥርዓቶችን ጨምሮ ሌሎች በክልሉ የሚገኙ የባሕል እሴቶችን ለማሳደግ ቢሮዉ በተናጠልና ከሌሎች አቻ ተቋማት ጋር በመሆን የተለያየ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ባሕላዊ እሴቶች ቀደምት መሠረታቸውን ጠብቀው እንዲቀጥሉ፣ እንዲለሙ፣ እንዲተዋወቁ፣ እንዲጠኑ እና ለልማት እንዲውሉ ለማደረግ እየተሠራ መኾኑንም አንስተዋል።
ከዚህ በፊት የተሠሩ እና አሁን ላይ እየተሠሩ ካሉ ሥራዎች መካከልም ሃይማኖታዊ እና በሕላዊ ኹነቶች በተገቢ እንዲካሄዱ ማድረግ አንዱ ተግባር መኾኑን ተናግረዋል።
ሀገር በቀል እሴቶች እውቅና እንዲሰጣቸው ማድረግ ሌላኛው ተግባር መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ባሕላዊ እሴቶች ላይ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች እና ሴቶች በንቃት እንዲሳተፉ ለማድረግ የግንዛቤ ፈጠራ እየተሠራ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ባሕላዊ እሴቶች ላይ ጥናቶች እንደሚሠሩም ጠቅሰዋል። ባሕላዊ የእርቅ ሥርዓት እና ሌሎች ባሕላዊ እሴቶች ላይ ተሳትፎ ለነበራቸው አካላትም እውቅና የተሰጠበት ኹኔታ መኖሩን አንስተዋል፡፡
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here