ባሕር ዳር: ጥቅምት 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ይስማ ንጉሥ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ ይገኛል። ከደሴ ተነስተን ወደ ወልድያ ከተማ 50 ኪሎ ሜትር ገደማ እንደተጓዝን ከዋናው መንገድ 4 ኪሎ ሜትር ወደ ግራ ገባ ብሎ ከአምባሰል ተራራ ግርጌ ላይ እናገኘዋለን፡፡
በዚሁ ሥፍራ ለዓድዋ ጦርነት መነሻ የኾነው የውጫሌ ውል ተፈርሞበታል። ይስማ ንጉሥ የሚለው ስያሜን ያገኘውም ከዚሁ ውል ጋር የተያያዘ እንደኾነ በታሪክ ይነገራል። በውጫሌ ውል አንቀጽ 17 ጣልያን የትርጉም ልዩነት ያለው ቃል በመጠቀም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለመጣስ ሴራ የጎነጎኑበት መኾኑን ታሪክ ይናገራል።
በወቅቱ ይህ የተጭበረበረ ውል እንዲፈርስ እቴጌ ጣይቱ ብጡል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ይነገራል፡፡ እቴጌ ጣይቱ የጣልያንን መሠሪ አካሄድ ሲረዱ ውሉ እንዲፈርስ ወስነው፤ ለሀገራቸው ክብርና ሉዓላዊነት ለመፋለም ቆርጠው ተነስተዋል።
እቴጌ ጣይቱ “እኔ ሴት ነኝ፣ ጦርነት አልወድም፤ ግን እንዲህ መሳዩን ውል ከምቀበል ጦርነት እመርጣለሁ” ብለው ለንጉሠ ነገሥቱ “ይስሙ ንጉሥ!” የሚል ታሪካዊ ንግግር አድርገዋል፡፡ ይህን ንግግራቸውን ተከትሎም የውጫሌ ውል የተጻፈበት ቦታ “ይስማ ንጉሥ” በሚል እንደተሰየመ ይነገራል፡፡
ከባለቤታቸው እና ከመኳንንቶቻቸው ጋር የመከሩት
አጼ ምኒልክም ውሉን ውድቅ በማድረግ የዓድዋ ጦርነትን ታሪካዊ የክተት አዋጅ አስነግረዋል፡፡ መላው ኢትዮጵያውያንም የክተት አዋጁን ተቀብለው ዘምተዋል። ጣልያንን በማንበርከክም የዓድዋ ጦርነትን በድል አጠናቅቀዋል። ይህ ድልም የአፍሪካውያን ድል ኾኖ በታሪክ ተመዝግቧል።
ይህ ታሪካዊ ቦታ ታሪኩ ተጠብቆ እና ለምቶ የኢትዮጵያውያንን አንድነት በሚዘክር መልኩ የቱሪስት መዳረሻ እንዲኾን የአማራ ክልል መንግሥት ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ የይስማ ንጉሥ ሙዚዬምን አስገንብቷል። ሙዚዬሙም በ2013 ዓ. ም ተመርቋል።
እቴጌ ጣይቱን እና አጼ ምኒልክን የሚዘክር ሐውልት ደግሞ በ2015 ዓ.ም በዚሁ ቦታ ላይ ተሠርቷል፡፡ በሙዚዬሙ በዓድዋ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያውያንን አንድነት፣ ጀግንነት፣ አልደፈር ባይነት እና ብሔራዊ ኩራትን የሚገልጹ የዓድዋ ድል አሻራዎችን አሰባስቦ በማሥቀመጥ ትውልድ እንዲማርበት ለማድረግ ፋይዳው የጎላ ነው።
የደቡብ ወሎ ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ አስያ ኢሳ ማኅበረሰቡ አካባቢው ለምቶ ወደ ቱሪዝም እንዲገባ ካለው ፍላጎት አንጻር መሬቱን በነጻ ሰጥቶ ሙዚዬሙ መገንባቱን አስታውሰዋል።
ግንባታው ከተጠናቀቀ በኋላ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ጉዳት ደርሶበት የቆየ መኾኑን ተናግረዋል። አሁንም በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ምክንያት በሚጠበቀው ደረጃ ሙዚዬሙን አልምቶ ወደ ሥራ ማስገባት አለመቻሉን አመላክተዋል።
ሙዚዬሙ በታሠበው ልክ ሥራ ቢጀምር በአካባቢው ካሉት የቱሪዝም መስህቦች ጋር በማስተሳሰር በቱሪዝም መዳረሻነት ሚናው የጎላ መኾኑን ጠቁመዋል። ለአካባቢው ማኀበረሰብም የሥራ ዕድል በመፍጠር የልማት ተጠቃሚ እንደሚያደርግም አመላክተዋል።
የአማራ ክልል ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኀላፊ አየለ አናውጤ (ዶ.ር) የሙዚዬሙ ዓላማ የዓድዋ ድል ታሪክን በማስታወስ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ መኾኑን ገልጸዋል።
ሙዚዬሙን ወደ ሥራ ለማስገባት በተለያየ ወቅት የተፈጠሩት የጸጥታ ችግሮች እንቅፋት እንደኾኑባቸው አንስተዋል። በዚህም ምክንያት ባለሙያዎች ተንቀሳቅሰው ሙዚዬሙን ማደራጀት እና ወደ ሥራ ማስገባት እንዳልተቻለም ነው የተናገሩት።
በ2018 በጀት ዓመት 16 ሚሊዮን ብር በመመደብ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት የደረሰውን ጉዳት ለመጠገን እና ተጨማሪ ግብዓቶችን በማሟላት ሙዚዬሙን አደራጅቶ ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
ሙዚየሙን ከፍ ባለ ደረጃ ሀገራዊ እና አሕጉራዊ ይዘት እንዲኖረው ተደርጎ ለማደራጀት እየተሠራ ነው ብለዋል። የቅርስ ማስቀመጫ እና ማሳያ ሾው ኬዝን ጨምሮ ሌሎች ቁሳቁስ ተገዝተው በጸጥታው ምክንያት ወደ ሙዚዬሙ ማስገባት እንዳልተቻለ ነው የገለጹት።
በሙዚዬሙ የዓድዋን ታሪክ የሚመጥን፣ በጦርነቱ ጥቅም ላይ የዋሉ የጦር መሣሪያዎች፣ ቁሳቁስ፣ መገልገያዎች እና መዛግብት ተደራጅተው እንደሚቀመጡበት ተናግረዋል።
እነዚህን ከዓድዋ ጦርነት ጋር ትስስር ያላቸው ሀገራዊ ቅርሶችን ለማሠባሠብም ብሔራዊ ኮሚቴ መቋቋሙን አስታውቀዋል። በዞን እና በክልል ደረጃም የጋራ ኮሚቴ በማዋቀር በየአካባቢው ያሉ ቅርሶችን ለማሠባሠብ እንቅስቃሴ መጀመሩን ነው የተናገሩት።
በየአካባቢው ያለው ማኀበረሰብ ከዓድዋ ድል ጋር ትስስር ያላቸውን ቅርሶች በማሠባሠብ ተሳትፎ እንዲያደርግ መልዕክት አስተላልፈዋል። በየግለሰቦች እጅ ያሉትን ቅርሶች በሙዚዬሙ ውስጥ በስማቸው ተመዝግበው በክብር እንዲቀመጡላቸው በየደረጃው ላለው የባሕል እና ቱሪዝም መዋቅር እንዲሰጡም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
            








