ተፈጥሮ ያስዋበው ድንቅ ሥፍራ- ኮሶዬ

0
29
ደባርቅ: ኅዳር 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎ኮሶዬ ከጎንደር ከተማ በሰሜን አቅጣጫ 3ዐ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ወገራ ወረዳ የሚገኝ ሥፍራ ነው። ቦታው ከባሕር ወለል በላይ 3 ሺህ ሜትር ከፍታ ላይ እንደሚገኝም ይገለጻል።
‎ኮሶዬ የሚገኝበት አካባቢ ከፍተኛ ቦታ ወይም ተራራማ በመኾኑ “ኮሶዬ አምባራስ” የሚል መጠሪያ ተሰጥቶታል፡፡ በተጨማሪም ስያሜው የተሰጠው በአካባቢ በርካታ የኮሶ ዛፍ ስለሚገኝ እንደኾነ ከወገራ ወረዳ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።
‎ቦታው በዓለም ቅርስነት ከተመዘገበው የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ጋር የተያያዘ ሰንሰለታማ ውብ፣ ለዓይን የሚማርኩ የመሬት ገጽታዎች፤ ዋሻዎች፣ ተራራዎች፣ ሸለቆዎች፤ ኮረብታዎች መገኛም ነው። በውስጡ እንደ ጅብ፣ አቦ ሸማኔ፣ ጭላዳ ዝንጀሮ፣ ድኩላ፣ ሚዳቋ፣ ጦጣ፣ ጉሬዛ እና የመሳሰሉ የዱር እንስሳት እና አዕዋፍት መገኛም ጭምር ነው።
‎አካባቢውን ነገሥታት ይጎበኙት፤ በውበቱም ይደነቁበት እንደነበር ይነገራል። አጼ ኃይለ ሥላሴ የእንግሊዟን ንግሥት ኤልሳቤጥ ጥር 11/1957 ዓ.ም ኢትዮጵያ በመጡ ጊዜም ካስጎበኟቸው ዋና ዋና የቱሪስት መዳረሻዎች መካከል አንዱ እንደኾነም በታሪክ ተቀምጧል።
በወቅቱ ‎ንግሥቷ ከመጡበት ሀገር የአየር ንብረት ጋር ተመሳሳይ እና ምቹ ኾኖ እንዳገኙት ለንጉሡ መግለጻቸውም ይነገራል። ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴም በቦታው ተፈጥሯዊ ውበት ከመማረካቸው የተነሳ ወደ ጎንደር ከተማ በሄዱ ቁጥር ሳይጎበኙት አይመለሱም ነበር ይባላል።
‎በኮሶዬ ጅብ ዋሻ በተባለ አካባቢ የጎንደር አብያተ መንግሥታት ሲገነቡ ለግንባታ አገልግሎት የሚውል ቀይ አፈር በብዛት ይጓጓዝበት እንደነበረም ይነገራል።
‎አካባቢው በጣልያን ወረራ ጊዜ ለአባት አርበኞች እንደ መጠለያ ኾኖ ማገልገሉም ይጠቀሳል። በደርግ ዘመነ መንግሥትም የሎጀስቲክስ ማከማቻ እና መምሪያ ኾኖ ያገለግል ነበር ይባላል።
የወገራ ወረዳ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አረፈዓይኔ ካሴ ቦታውን ለማስተዋወቅ እና የቱሪስት መዳረሻነቱን ለማሳደግ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ሁለት የእንግዳ ማረፊያ ሎጅዎች በግንባታ ላይ እንደሚገኙም አንስተዋል።
ከ28 በላይ የሚኾኑ የአካባቢው ወጣቶችን በማሥተባበር እና የስካውት ቡድን በማቋቋም አካባቢውን ለማስተዋወቅ እና ለመጠበቅ እየተሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል። ቦታው ከጎንደር ከተማ በቅርብ ርቀት የሚገኝ መኾኑ ለጎብኝዎች ተመራጭ እንደሚያደርገውም ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ከ35 በላይ ለሚኾኑ ሰዎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም አንስተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here