የተፈጥሮ አዳራሽ የኾነው የፈርጣጣ ዛፍ ዋሻ

0
36
ባሕር ዳር፡ ኅዳር 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ)ፈርጣጣ ዛፍ በቆላማ አካባቢዎች የሚበቅል ብዙ ቅጠሎች እና ቅርንጫፎች የሌሉት ግንደ ወፍራም የዛፍ ዓይነት ነው፡፡
የፈርጣጣ ዛፍ በኢትዮጵያ ከሚገኝባቸው አካባቢዎች መካከል አማራ ክልል አንዱ ነው። በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ደግሞ በስፋት ይገኛል፡፡
የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር የባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ባለሙያ አለፈ ዋኘው ፈርጣጣ ዛፍ በዞኑ ቆላማ አካባቢዎች በብዛት እንደሚገኝ ነግረውናል።
ከዞኑ ከተማ ሰቆጣ በስተሰሜን አቅጣጫ 42 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በዝቋላ ወረዳ ፅፅቃ ከተማ የሚገኘው የፈርጣጣ ዛፍ ዋሻ ደግሞ ትልቁ እና ልዩው እንደኾነ ነው የገለጹልን። ዛፉ ወደ ላይ አንድ ወጥ እና ልሙጥ ነው ይላሉ።
የፈርጣጣ ዛፍ ዋሻ ከሌሎች ዛፎች ልዩ የሚያደርገውም የዛፉ ውፍረት ከ40 እስከ 50 ሜትር የሚደርስ መኾኑ ነው። በዛፉ ውስጥ ያለው የተፈጥሮ ዋሻም ከ37 እስከ 40 ሰዎች መያዝ የሚችል መኾኑ ሌላው ልዩ የሚያደርገው ጉዳይ መኾኑን አንስተዋል።
ይህ ዋሻ በደርግ እና በኢህአዴግ ጊዜያት የመሠብሠቢያ አዳራሽ፣ የትልልቅ ጦር መሣሪያ ማከማቻ እና ስንቅ ማስቀመጫ ኾኖ ማገልገሉንም ተናግረዋል። ለአካባቢው ማኅበረሰብም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የዝናብ እና ፀሐይ መጠለያ ኾኖ ማገልገሉንም ገልጸዋል።
የዛፍ ዋሻው ተፈጥሯዊ ስሪት ያለው፣ በሰዎች ማሻሻያ ያልተደረገበት እና ያልተነካካ መኾኑንም ተናግረዋል። የተቦረቦረ መግቢያ በር፣ መስኮት መሰል ክፍተቶች እና እንደ ኮርኔስ የተለጠፈ ቅርፊት ያለው ጣሪያ ያለው ነው።
የውስጠኛው ክፍል በእጅ የተሠሩ የሚመስሉ መቀመጫ ወንበሮች፣ እቃ ማስቀመጫዎች፣ ጥርብ ድንጋይ የሚመስል ወጣገባ ግድግዳ እና ወለል እንዳለውም ጠቅሰዋል። ከመሬት ወደ ላይ ዋሻው ቁመቱ ስድስት ሜትር እንደኾነም ይነገራል።
የወለሉ ስፋት ደግሞ 12 ሜትር ነው። የፈርጣጣ ዛፍ ፍሬ ቅል መሰል ሲኾን ውስጡ ለምግብነት ከዋለ በኋላ የላይኛው ክፍል ለውኃ መቅጃ እና መጠጫነት እንደሚያገለግልም ይገለጻል።
የፈርጣጣ ዛፍ ዋሻ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች መደረሻ ሁኖ እያገለገለ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ሁልጊዜም ለጎብኝዎች ክፍት መኾኑንም ገልጸዋል። ሃይማኖታዊ የንግሥ በዓላት እና መንግሥታዊ ሁነቶች በከተማዋ ሲኖር የጎብኝዎች ቁጥር እንደሚጨምርም ጠቅሰዋል።
የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ እና የዝቋላ ወረዳ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቱሪስት መዳረሻውን የማልማት እና የማስተዋወቅ ሥራዎች እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ለጎብኝዎች ምቹ እንዲኾን የሚያደርጉ ሥራዎች መሠራታቸውንም ገልጸዋል። ከሰው እና እንስሳት ንክኪ ነጻ ለማድረግም የአጥር እና የጥበቃ ሥራ መሠራቱን ጠቅሰዋል። የአካባቢው ማኅበረሰብም ልዩ ጸጋው እንደኾነ በመረዳት እንክብካቤ እንደሚያደርግለት ነው የጠቀሱት። ለቱሪዝም ያለውን ፋይዳ ግን የመረዳት ውስንነቶች አሉ ነው ያሉት።
የመሠረተ ልማት ሥራዎች እና ለጎብኝዎች ማረፊያ የሚኾኑ አገልግሎት መስጫዎች ከቱሪስት መዳረሻው አቅራቢያ እንዲኖር ለማድረግ እየተሠራ እንደኾነም ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here