የክብር ልብሱ በርኖስ

0
60
ባሕር ዳር: ኅዳር 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎‎በርኖስ በሰሜን ሸዋ መንዝ እና በሌሎችም የአማራ ክልል ደጋማ አካባቢዎች የሚለበስ ካፖርት መሳይ ልብስ ነው፡፡
በርኖስ ከበግ ጸጉር የሚሠራ፣ ቀለሙ ጥቁር፣ አንገትጌ እና በግራ በኩል ተገጥሞ ያልተሰፋ፤ በቀኝ ትከሻ ላይ ደግሞ ረዘም ሾጠጥ ያለ እጅጌ መሳይ ያለው ባሕላዊ ልብስ ነው፡፡ እጅጌ መሳዩ የመሣሪያ አፈሙዝ ደግፎ ለመያዝ ያገለግላል፡፡
ለጌጥ እና ለምቾት አንገትየው እና ጠርዙ በባለቀለም ጨርቆች እንዲጌጥ ይደረጋል ይላል ከሰሜን ሽዋ ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በርኖስ የሚሠራውም ከጥቁር ጠቦት በግ ጸጉር ነው፡፡ ደጋግሞ ከተሸለተ በግ የሚገኘው ጸጉር ጠንካራ ስለሚኾን በርኖሱ ይሻክራል፤ ይኮሰኩሳል፤ ስለኾነም ለበርኖሱ ልስላሴ ጸጉሩ ለስላሳ ከኾነ ጠቦት በግ ላይ ተሸልቶ ይዘጋጃል፡፡
የበጉ ጸጉር እንደ ጥጥ ተባዝቶ እና ተፈትሎ የሚዘጋጅ ሲኾን እንደ ድር እና ማግ ተጋምዶ በመሸመንም ይዘጋጃል፡፡ የሽመናው ሂደት ለጥንካሬ እና ልስላሴው በውኃ በመታጠብ እና በመረገጥ ሂደቶች ውስጥም ያልፋል፡፡
ተሸምኖ የተዘጋጀው የበርኖስ “ጣቃ” በሚለብሰው ሰው ልክ ተመጥኖ በመቅደድ ይዘጋጃል፡፡ በአንገትየው እና በጠርዙ ዙሪያ ለጌጥ እና ለገበር የሚያገለግል በክፈፍነት የሚሰፋበት የጨርቅ አይነት አለው፡፡
በርኖስ በቀዝቃዛ አካባቢዎች እና በቀዝቃዛ ጊዜ ይለበሳል፡፡ ታዋቂ ግለሰቦች እና የሀገር ሽማግሌዎች በበዓላት፣ በሰርግ፣ በሕዝባዊ በዓላት ይለብሱታል፡፡ በደስታ ጊዜ ታላላቅ ሰዎች እና ሙሽሮች የሚለብሱት ሲኾን በሀዘን ጊዜደግሞ ማንኛውም ሰዎች ይለብሱታል፡፡ አለባበሱም ተገልብጦ ነው፡፡
በርኖስ የታላላቅ ሰዎች የክብር ልብስ ሲኾን የታላላቅ ሰዎች ሚስቶች፣ በሰርግ ወቅት ሴቷ ሙሽራ ከወላጆቿ ቤት ወደ ወንዱ ስትሄድ፣ በሽምግልና ጊዜ እና በሌሎች የክብር ቦታዎች፣ በቅርብ ዘመድ ሞት ሀዘንን ለመግለጽ ይለበሳል፡፡
በልደት (የገና) በዓል በርኖስ በመልበስ ገናን መጫዎትም የኢትጵያውያን ባሕል እስከመኾን የደረሰ ተዛምዶ አለው፡፡
ኢትዮጵያውያን ለሚያከብሩት እና ለሚሸልሙት ሰው ካባ፣ ጦር፣ ጎራዴ እና ሌሎች ቁሳቁሶችን እንደሚሸልሙት ሁሉ የመንዝ እና አካባቢው ነዋሪዎችም ለክብር እንግዳቸው በርኖስ ይሸልማሉ፡፡ እናም በርኖስ በመንዝ ብሎም በሰሜን ሸዋ ዞን ታላቅ የክብር ልብስ ነው፡፡ የቀደምት አባቶችን ጥበብ እና ታሪክም ይዘክራል፡፡
በርኖስ በአሁኑ ወቅት መሠራቱም ኾነ መለበሱ እየቀነሰ ነው፡፡ የሚለብሱት የኅብረተሰብ ክፍሎችም ጥቂት ናቸው፡፡ በርኖስን የሚሠሩ ሰዎች በዕድሜያቸው ምክንያት ሲያልፉ ተተኪ አለመኖር፣ ሥራው ረጅም ጊዜ የሚፈልግ እና አድካሚ መኾኑ፣ እንዲሁም እንደ ብርድ ልብስ ያሉ ተኪ አልባሳቶች መስፋፋት ለበርኖስ መመናመን በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡ በመንዝ ማማ ወረዳ በአንጻሩ በተሻለ ሁኔታ እንዳለ ይገለጻል፡፡
በርኖስ እንደዛሬው ቴክኖሎጂ ባልነበረበት ዘመን ጥጥ ተዘጋጅቶ እና በሸማ ሥራ ሂደት አልፎ ብርድን ለመከላከል ብሎም ለክብር ይለበስ የነበረ ባሕላዊ ልብስ ነው፡፡
በዋሴ ባዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here