የቱሪዝም ልማት

0
113
ባሕር ዳር: ኅዳር 19/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገቡትን ጨምሮ በርካታ ብርቅ እና ድንቅ የቱሪስት መስህቦች ባለቤት ናት፡፡
አማራ ክልልም የበርካታ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ሃብት መስህቦች ባለቤት ነው፡፡
✍ ለመሆኑ በዚህ ዓመት በአማራ ክልል ቱሪዝምን በማጠናከር ተጠቃሚነት ለማሳደግ ምን እየተሠራ ይኾን?
የቅዱስ ላሊበላ እና አካባቢው አስጎብኚዎች ማኅበር ጸሐፊ ዲያቆን ሙጫው ደረበ በላሊበላ ከተማ እና ቅዱስ ላሊበላ ገዳም የልደትን በዓል ለማክበር ዝግጅት መጀመሩን ጠቅሰዋል፡፡
የላሊበላ ከተማ እና አካባቢው ሕዝብ አማኙን ለመቀበል ምክክር ተደርጎ እና ገንዘብ ተዋጥቶ መጠናቀቁንም ነግረውናል።
ወጣቶቹም እግር የማጠብ፣ ማረፊያ ቦታ የማመቻቸት እና በማመላከት እንዲሁም የአካባቢውን ደኅንነት በመጠበቅ ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
አስጎብኝዎችም እንግዶች የበዓሉን ታሪክ፣ ኪነ ሕንጻውን፣ የሕዝቡን ባሕል እና እሴት እንዲያውቁ ለማድረግ በዕውቀት እና ክህሎት ተዘጋጅተው እየጠበቁ ናቸው።
እንግዶች ተመችቷቸው ይቆዩ ዘንድ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር፣ እቃ እንዳይጠፋባቸው፣ እንዳይዋከቡ በመከላከል፣ ገንዘብ የሌላቸውም ማደሪያ እንዲያገኙ እና የደኅንነት ስጋት እንዳይገባቸው በማድረግ በትብብር እንሠራለን ነው ያሉት።
ቱሪስት ለላሊበላ ሕዝብ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ነው። ይህንኑ አጠናክሮ ለማስቀጠል አስጎብኝዎች፣ ኮሚቴዎች፣ የከተማው ነዋሪዎች እና የገዳሙ አደረጃጀት በሙሉ በዓሉን በተለመደው ሰላማዊ እና መንፈሳዊ ኹኔታ ለማክበር ዝግጅቱ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
በአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር መልካሙ አዳም ቱሪዝም ልማት እና ሰላም ተመጋጋቢ ገጽታዎች መኾናቸውን ተናግረዋል።
ቱሪዝም ሰላም እና መሠረተ ልማቶችን እንደሚፈልግ ሁሉ፤ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ባለባቸው አካባቢዎች ልማቶች መኖራቸውንም አመላክተዋል።
ለቱሪዝሙ ሲባል የሚሠሩ ልማቶች ማኅበረሰቡንም ይጠቅማሉ ያሉት ዳይሬክተሩ ልማቶች ሰው ሠራሽ መስህብን እና ቱሪዝምን እንደሚፈጥሩም አብራርተዋል።
ሰላም ለቱሪዝም አስፈላጊ መኾኑን ጠቅሰው ሰላም በጠፋበት አካባቢም ቱሪዝም ሰላም ሊፈጥር እንደሚችል አንስተዋል።
የአማራ ክልል ቱሪዝም ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ ተግዳሮቶች እንደገጠሙት አንስተዋል። ችግሩን በመቋቋም ቱሪዝሙን ለማሳደግ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል።
በዚህ ዓመት ቱሪዝሙን በማነቃቃት ሕዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን ተናግረዋል።
የክልሉን ገጽታ በመገንባት እና በማስተዋወቅ፣ በቅርስ ጥገና፣ ዋናዎቹን ክብረ በዓላት የሚዲያ ሽፋን በማሰጠት፣ በዓላትን በኮሚቴ አስተባባሪነት በመፈጸም በዚህ ዓመት የተሻለ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑን አመላክተዋል።
የቱሪስቶችን ቆይታ ለመጨመር እና ገጽታን ለመገንባት ለአገልግሎት ሰጭዎች ግንዛቤ እየተፈጠረ መኾኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። የተጋነነ የአገልግሎት ዋጋ እንዳይጠየቅ፣ ቱሪስቶችን በመንከባከብ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን በመፍጠር ለተወዳዳሪነት በትኩረት እየተሠራ ነውም ብለዋል።
የጎንደር አብያተ መንግሥታት ጥገና፣ የጎርጎራ እና የሎጎ ሐይቅ ግንባታን ጨምሮ የመስህብ ሃብቶች ጥገና እና የግንባታ ሥራዎች መዳረሻዎችን በማብዛት የቱሪስቶችን ፍሰት በመጨመር፣ ቆይታቸውን በማራዘም እና አስደሳች በማድረግ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
የጎርጎራ ኢኮ ሪዞርት መጠናቀቅ፣ የጣናነሽ ቁጥር ፪ ጀልባ ሥራ መጀመር፣ በሐይቅ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የቱሪስት አገልግሎት ፕሮጀክት መጀመር የክልሉን ቱሪዝም የበለጠ እንደሚያጠናክረው አመላክተዋል።
በጣና ሐይቅ ዙሪያ የዳጋ እስጢፋኖስ የእንግዳ መቀበያ፣ የደቅ ደሴት ወደብ፣ ዘጌ ላይ የሚሠራው የቱሪስት ገበያ ተጠናቅቀው ወደ ሥራ ሲገቡ ዘርፉን በማሳደግ እና በማስፋት የሕዝብን ተጠቃሚነት እንደሚያሰፉም አመላክተዋል።
የጎንደር አብያተ መንግሥታት ጥገና መጠናቀቅ ጋር ተያይዞ ጎብኝዎችን በቅጥር ግቢው ማቆየት የሚያስችል አሠራር በመነደፉ በአብያተ መንግሥታቱ ይከወኑ የነበሩ ሥርዓቶችንም ለማስተዋወቅ እንደሚሠራ ጠቁመዋል።
በዩኔስኮ የተመዘገቡ ሦስት የቱሪስት መዳረሻዎች እና በምዝገባ ሂደት ላይ ያለው የጣና ሐይቅ እርጥበት አዘል ቦታዎችን ጨምሮ ሌሎችም መዳረሻዎችን በማልማት የክልሉን ሕዝብ ከዘርፉ ተጠቃሚ የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
ይህንን ጭስ አልባ ኢንዱስትሪ በማልማት እና በማስፋት የበለጠ ተጠቃሚ ለመኾን ሕዝቡ ለሰላም፣ ለመስህቦች ልማት እና ጥበቃ ትኩረት ሰጥቶ መሥራትም ይጠበቅበታል።
ዘጋቢ፦ ዋሴ ባየ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here