ባሕር ዳር: ኅዳር 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የባኩሳ ብሔራዊ ፓርክ በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በጃዊ ወረዳ ውስጥ ይገኛል፡፡
ፓርኩን በምዕራብ ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል፣ በምሥራቅ ባኩሳ ኪዳነ-ምህረት ቀበሌ፣ በሰሜን ባኩሳ ማርያም ቀበሌ እና በደቡብ ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል እና ባኩሳ ማርያም ቀበሌ ያዋስኑታል፡፡
የባኩሳ ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ በላቸው ማሩ ፓርኩ 51 ሺህ 796 ሄክታር መሬት ስፋት አለው ብለዋል፡፡
ፓርኩ ሙሉ በሙሉ የቆላማ የአየር ንብረት ውስጥ ይገኛል፡፡ በሀገራችን በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ የተመናመነ የበረሃ ብዝኀ ሕይወት ውስጥ ወካይ ሥርዓተ ምኅዳር የተፈጥሮ ደን ሲኾን ከ80 በመቶ በላይ ተፈጥሮሯዊነቱን የጠበቀ ነው ብለዋል፡፡
ከ28 በላይ ታላላቅ አጥቢ የዱር እንስሳት፣ ከ31 በላይ አእዋፋት እና ከ58 በላይ የዛፍና ቁጥቋጦ እና በርካታ የሳር ዝርያዎች ይገኙበታል፡፡ ተሳቢ እና ተራማጅ እንደ ዘንዶ፣ አዞ፣ የተለያዩ የእባብ ዝርያዎችም ይገኙበታል ነው ያሉት፡፡
በፓርኩ የተፈጥሮ ደን በሀገሪቱ እና በክልሉ በብዛት የማይገኙ እፅዋት እንደ ሽመል፣ ጥቁር እንጨት፣ የቆላ ዋንዛ፣ ኮመር፣ የእጣን ዛፍ፣ ዶቅማ፣ ላሎ፣ ዋርካ፣ ሾላ ዛፎች መገኛ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
አንበሳ፣ የቆላ አጋዘን፣ ድኩላ፣ ከርከሮ፣ ዝንጀሮ፣ ፌቆ፣ ነብር፣ ጉሬዛ፣ ቀይ ጦጣ፣ ተኩላ፣ ሚዳቋ፣ ጅብ፣ ጀርባው ጥቁር ቀበሮ፣ በፓርኩ ውስጥ የሚገኙ የዱር እንስሳት መኾናቸውን ኀላፊው ተናግረዋል፡፡
ፓርኩ በቆላማ አካባቢ የሚገኝ እና ሰሊጥ እና አኩሪ አተር አብቃይ በመኾኑ ከተለያዩ አካባቢዎች እና ከአጎራባች ክልሎችም በሚመጡ ሰዎች ሕገ ወጥ እርሻ ለፓርኩ ፈታኝ ሁኔታ ነው ብለዋል፡፡ ሕገወጥ አደን፣ ዕጣን እና ሙጫ ለቀማ ሌሎች የፓርኩ ችግሮች እንደኾኑ ገልጸዋል፡፡
መንግሥት በጀት መድቦ ፓርኩን የሚጠብቁ 36 ስካውቶችን ጨምሮ 72 የፓርክ ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች በሥራ ላይ መኾናቸውን አንስተዋል፡፡
አሁን ላይ ፓርኩን ለመጠበቅ ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት የጥበቃ ሥራዎችን ለመሥራት በክልሉ ያለው የጸጥታ ችግር ዋነኛ ችግር ነው ብለዋል፡፡
ለወደፊት ፓርኩ ወደ ጉብኝት እንዲገባ በርካታ ሥራዎችን ይጠይቃል ነው ያሉት፡፡ ትምህርት ቤቶች ላይ ክበባትን በማደራጀት ስለፓርኩ እና ጥበቃው ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑን አንስተው ከእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ እየሠሩ ስለመኾኑም አብራርተዋል፡፡
የፓርኩ መጠበቅ ለጥናት እና ምርምር፣ ለቱሪዝም፣ ወጣቶችን በማደራጀት በዕጣን እና ሙጫ ለቀማ በንብ ማነብ ላይ የሥራ ዕድል ይፈጥራል ነው ያሉት፡፡
በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሕይወት ትምህርት ክፍል ኀላፊ አዕምሮ መኮንን (ዶ.ር) ከፓርክ ጽሕፈት ቤቱ ጋር የጋራ ስምምነት ወስደው ከዚህ በፊት የብዝኀ ሕይወቱን ጥናት መካሄዱን አንስተዋል፡፡
በቱሪዝም ትምህርት ክፍል የኢኮ ቱሪዝም ማዕከል እንዲኾን ጥናት መደረጉን እና ለዩኒቨርሲቲው የጥናት እና ምርምር ማዕከል እንዲኾን እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ ለፓርክ ጥበቃ ሥራው ማኅበረሰቡን ግንዛቤ የማስጨበጥ፣ በጥናትና ምርምር እና ሥልጠና ላይ በጋራ እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡
በአማራ ክልል ደንና አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የዱር እንስሳት ጥናት እና ጥበቃ ዳይሬክተር አበባው ዓባይነህ (ዶ.ር) የባኩሳ ብሔራዊ ፓርክ በክልሉ ከሚገኙት ብሔራዊ ፓርኮች አንዱ ነው ብለዋል፡፡
ፓርኩ ከ15 ዓመት በፊት እውቅና ተሰጥቶታል፤ ይሁንና በፓርኩ ውስጥ ሕገወጥ ሰፈራ እና እርሻ እንደሚካሄድ አንስተዋል፡፡ ችግሩን በቅንጅታዊ አሠራር ለመፍታት የጸጥታ ችግሩ አላስቻለም ነው ያሉት፡፡
ፓርኩ ከፍተኛ በጀት እና የሰው ኀይል የተመደበለት ቢኾንም በማልማት እና በመጠበቅ የተሠራው ሥራ በሚፈለገው ደረጃ አለመኾኑን ጠቁመዋል፡፡
ብሔራዊ ፓርኮች እና ጥብቅ ሥፍራዎች የውኃ ቋት በመኾናቸው ወንዞች እንዳይደርቁ፣ ብዝኀ ሕይወትን እና የአየር ንብረትን በመጠበቅ ሚናቸው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
ከደን ውጤቶች በተጨማሪ ወደ ቱሪዝም ገበያ ሲገቡ ለማኅበረሰቡ የሚሰጡት ጠቀሜታ ከፍ ያለ መኾኑን አንስተዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ ብሔራዊ ፓርኮች እና ጥብቅ ሥፍራዎችን ለመጠበቅ የወሰን ግፊ፣ ደን መመንጠር፣ ሕገ ወጥ አደን እና የእሳት አደጋዎች ዋና ዋና ችግሮች ናቸው ብለዋል፡፡
ጥብቅ ሥፍራዎች ተጠብቀው ለማኅበረሰቡ እንዲጠቅሙ ስለጥበቃው የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ሕገወጥ ተግባራት ሲኖሩ አጥፊዎች ወደ ሕግ ቀርበው እንዲታረሙ ለማድረግ እየተሠራ ነው፤ ማኅበረሰቡም ይህንን አውቆ ለጥብቅ ሥፍራዎች መጠበቅ የበኩሉን እንዲያበረክት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!







