ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ጥንታዊቷን መርጡለ ማርያም ቤተክርስቲያንን ጎበኙ።

0
43
ደብረ ማርቆስ: ኅዳር 27/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ጥንታዊቷን ርዕሰ ርዑሳን መርጡለ ማርያም ቤተክርስቲያንን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ.ር)፣ የምሥራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ፣ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እዝ አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ብርሃኑ ጥላሁንን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
ርዕሰ ርዑሳን መርጡለ ማርያም ቤተክርስቲያን በኢትዮጵያ ከሚገኙ ጥንታዊ አብያተክርስቲያናት መካከል አንደኛዋ ናት። የጥንት ዘመን ታሪክን ያቀፈችው መርጡለ ማርያም በኢትዮጵያ ስማቸው ጎልቶ ከሚነሱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ትጠቀሳለች።
በወንድማማቾቹ ነገሥታት በአብረሃ ወአጽብሐ ዘመነ መንግሥት እንደተገነባች የሚነገርላት ርዕሰ ርዑሳን መርጡለ ማርያም ቤተክርስቲያን የጥንታዊ ነገሥታት ቅርሶችን፣ ንዋየ ቅድሳትን፣ የብራና መጻሕፍትን ጨምሮ አያሌ ጥንታዊ ቅርሶችን ይዛለች።
ይህች ጥንታዊት ቅድስት ስፍራ ከታሪኳ ሳትጎድል ከትውልድ ትውልድ ተሸጋገር ዘንድ ጥበቃ እና እንክብካቤ ያስፈልጋታል።
የርዕሰ ርዑሳን መርጡለ ማርያም ቤተክርስቲያን አሥተዳዳሪ ርዕሰ ርዑሳን አባ ብርሃነ መስቀል አንዳርጌ የቤተክርስቲያኗ ጥንታዊ ቅርሶችን ለመጠበቅ የሙዚዬም ግንባታ እየተካሄደ መኾኑን ተናግረዋል። የሙዚዬሙ ግንባታ እንዲጠናቀቅ እና የቤተ ክርስቲያን ጥንታዊ ቅርሶች እንዲጠበቁ የክልሉ መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ጥንታዊ ቅርሶችን የያዘችው እና ትናንትን ለዛሬ የምታሳየው ቤተክርስቲያኗ እንድትጠበቅ ከሁሉም ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል።
የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳደር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር) መንግሥት ጥንታዊ ቅርሶች እንዲጠበቁ፣ እንዲጠገኑ እና ለትውልድ እንዲተላለፉ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል። ጥንታዊ ሥፍራዎች የጎብኚዎች መዳረሻ መኾን እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።
የጥንታዊቷ ርዕሰ ርዑሳን መርጡለ ማርያም ቤተክርስቲያን ቋሚ ቅርሶች እንዲጠገኑ እና ተንቀሳቃሽ ቅርሶች እንዲጠበቁ መንግሥት ይሠራልም ነው ያሉት።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here