ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 03/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ቤተ ክርስቲያኑ ከዓድዋ ታሪክ ጋር በእጅጉ የተሣሠረ ታሪክ አለው፡፡ በዚህም የተነሣ በሁለተኛው የፋሽስት ወረራ ጊዜ እንደ ጦር ወንጀለኛ ተቆጥሮ ዋጋ ከፍሏል ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ቤተ ክርስቲያኑ ደረጃውን በጠበቀ እና ልዩ ልዩ ባለሙያዎችን ባሳተፈ መልኩ እየታደሰ መኾኑን እንደተመለከቱ ተናግረዋል።
የዓድዋ ሙዚየም በአካባቢው መገንባቱ፣ ለዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ ጥገና መደረጉ እና የመመልከቻ አምፊ መሠራቱ የአካባቢውን የቱሪዝም ፍሰት ከፍ አድርጎታል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ማዕከል እየኾነም ገልጸዋል፡፡
አሁን የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ (አራዳ ጊዮርጊስ) ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ እና ግቢ ታሪካዊ እና ዘመናዊ በኾነ መንገድ መታደሱ ደግሞ ታሪኩን የተሟላ እንዲኾን ያደርገዋል ነው ያሉት፡፡
የሕንጻው የአሠራር ጥበብ፣ የሥዕሎቹ ጥበባዊ ከፍታ፣ የብረት ሥራዎች የጥበበ እድ እና የጥራት ደረጃ እንዲሁም የቅርሶቹ የላቀ ዋጋ እጅግ አስደናቂ ኾኖ አግኝተነዋል ብለዋል፡፡
የቤተ ክርስቲያኑ እና የአካባቢው ጥገና አሁን ከጀመርናቸው የከተማ ማዘመን ሥራዎች፣ የቱሪስት መዳረሻዎች እና የቅርስ አጠባበቅ ደረጃዎች ጋር ተጣጥሞ እንዲሠራ፣ የሚመለከታቸው ሁሉ የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽዖ እንዲያደርጉ አደራ ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!








