የጣና ሐይቅ ደሴተ ገዳማት እና አዋሳኝ ባሕረ ሸሽ መልክዓ ምድርን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ሥራዎች እየተሠሩ ነው።

0
62
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ በጣና ሐይቅ ገዳማት እና አዋሳኝ ባሕረ ሸሽ መልክዓ ምድር የተፈጥሮ እና የባሕል እጩ ዓለም አቀፍ ቅርስ የምዝገባ ሂደት በተመለከተ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ምክክር አድርጓል።
በምክክር መድረኩ ላይ የተሣተፉት ከጎርጎራ ደብረ ሲና ማርያም አንድነት ገዳም የመጡት አባ ገብረ ማርያም ኪዳነ ማርያም ጣና ትልቅ ሀብት ነው፤ ገዳማት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሎም የዓለም የሚስጥር ቤት ናቸው ብለዋል።
ጣናን በዩኔስኮ ስናስመዘግብ ገዳማቱን በጥሩ ሁኔታ እና ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ማስተዋወቅ ይገባል፤ በዚህም ደግሞ ሁላችንም ደስተኞች ነን ብለዋል።
ሌላው በውይይቱ ተሳታፊ የነበረው የባሕር ዳር እና አካባቢዋ አስጎብኚ አሠፋ መላኩ ታላቁ ሐይቅ ጣና በዩኔስኮ መመዝገቡ ከክልልም አልፎ ለሀገር ብሎም ለአፍሪካውያን ኩራት ነው ብሏል።
የጣና ሐይቅ ደሴተ -ገዳማት ዓለም አቀፍ ቅርስ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ማዕከል ዓለም አቀፍ የተፈጥሮ እና የባሕል መካነ ቅርስ ኾኖ ሲመዘገብ በርካታ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ይኖሩታልም ብሏል።
የቱሪስት ፍሰቱን ከመጨመር ባለፈ ሀገራችን ኢትዮጵያዊ ዘርፈ ብዙ ባሕላዊ እና ተፈጥሯዊ ቅርስ ባለቤት መኾኗን የምናፀባርቅበት አንዱ ማሳያ ነው ብሏል። ማኅበረሰቡ ለዚህ በጎ ዓላማ የበኩሉን መወጣት እንዳለበት መኾኑን ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ምክትል ቢሮ ኀላፊ አየለ አናውጤ (ዶ.ር) ጣና ባለ ብዙ ፀጋ መኾኑን አውስተዋል። ጣና ሐይቅ ብቻ አይደለም ጣና ታሪክም፣ እምነትም፣ ቅርስም ባሕልም ነው ያሉት።
የጣና ሐይቅ ደሴተ-ገዳማት እና አዋሳኝ ባሕር ሸሽ መልክዓ ምድር በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባሕል ድርጅት ዓለም አቀፍ ቅርስ ኾኖ እንዲመዘገብ በርካታ ሥራዎች ሲሠሩ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡
የጣና ሐይቅ ደሴተ-ገዳማት እና አዋሳኝ ባሕር ሸሽ መልክዓ ምድር ዓለም አቀፍ ቅርስ ኾኖ ሲመዘገብ ሀብቱን ለዓለም ለማስተዋወቅ፣ ዘላቂ የኾነ የቅርስ ጥበቃ እና እንክብካቤ እንዲኖር ለማድረግ፣ የሀገርን እውቅና ከፍ ለማድርግ ሰፊ ሚና አለው ብለዋል።
በቅርሱ የመጀመሪያ ተጠቃሚዎቹም ተጎጅዎቹም የአካባቢው ማኅበረሰብ እንደኾነ የገለጹት ምክትል ቢሮ ኀላፊው ለዚህም ማኅበረሰቡ በሚደረገው ማንኛውም እንቅስቃሴ ቀዳሚ ተዋናኝ መኾን እንዳለበት ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- ሰመሀል ፍስሀ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here