ክልሉ ቀጣዮቹን በዓላት መሠረት አድርገው ወደ አካባቢው የሚገቡ እንግዶቹን ለመቀበል ተዘጋጅቷል።

0
73
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ክልል የበርካታ ቅርስ እና የብዙ የተፈጥሮ መስህቦች ባለቤት ነው። ክልሉ ለቱሪስቶች የተመቹ የመሠረተ ልማቶች ባለቤትም ነው።
በተለይ ከታኅሣሥ ወር መጨረሻ ጀምሮ በጥር ወር በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኝዎችን የሚስቡ በዓላት በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ይከናወናሉ።
ልደትን በላሊበላ እስከ ጥምቀትን በጎንደር፣ ጥርን በባሕር ዳር እስከ አገው ፈረሰኞች በዓል ክልሉን ለሚጎበኙ እንግዶች የማይረሳ ትዝታን የሚሰጡ ድንቅ ክዋኔዎች ይካሄዱበታል።
የአማራ ክልል ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ኀላፊ መልካሙ ፀጋዬ ከታኅሣሥ ወር መጨረሻ እስከ ጥር ወር መጨረሻ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ በዓላት በአደባባይ እንደሚከበሩ አውስተዋል።
ቢሮ ኀላፊው በዓሉ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስቶች በብዛት በተገኙበት በድምቀት የሚከበር በመኾኑ ቀደም ብሎ ሰፊ የዝግጅት ሥራ ሲከናወን ቆይቷል ብለዋል።
በዓሉን በድምቀት ማክበር እንዲቻልም ክልሉ ከሰሜን ወሎ ዞን ላሊበላ ከተማ እና ከጎንደር ከተማ አሥተዳደሮች በተጨማሪ ከተለያዩ ዞኖች እና ከወረዳዎች ጋር በቅንጅት መሥራቱን ጠቅሰዋል።
እንደ ክልል ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት የሚመጣው ቱሪስት ተመችቶት ክልሉን ጎብኝቶ እንዲመለስ እና የጎብኝት ጊዜውን እንዲያራዝም የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ተሟልተው የቱሪስቶች መግባት እየተጠበቀ ነው ብለዋል።
የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት አገልግሎት ሰጭ ሆቴሎች፣ ካፍቴሪያዎች እና አስጎብኚዎች የተሳለጠ አገልግሎት እንዲሰጡ ዝግጁ መደረጋቸውንም ጠቁመዋል።
ክልሉ ላይ በተቀናጀ መልኩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጥምረት ሥራ መሠራቱንም አስረድተዋል።
ከጸጥታ አንፃርም ምንም አይነት እንኳን እንዳይገጥም በርካታ ሥራዎች በዘርፉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተሠርቷል ብለዋል።
በዓሉ ተከብሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ የድጋፍ እና ክትትል ተግባሮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቢሮ ኅላፊው ተናግረዋል።
የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስቶች ክልሉን በመጎብኘት ጥሩ ጊዜን እንዲያሳልፉም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ሰመሀል ፍስሀ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here