ባሕር ዳር፡ ታኅሣሥ 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ ጥር 11 የሚከበረው የጥምቀት በዓል በመላው ኢትዮጵያ በልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ትዕይንቶች ታጅቦ በድምቀት የሚከበር በዓል ነው፡፡
በዓሉ በድምቀት ከሚከበርባቸው ከተሞች መካከል ጎንደር ቀዳሚዋ ናት። አጼ ፋሲለደስ በቀሀ ወንዝ ዳርቻ ያስገነቡት መዋኛ ገንዳ ደግሞ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከሚከበረው የተለዬ እንዲኾን አንድ ምክንያት ኾኗል።
ጥምቀተ ባሕሩ ታሪክ በማቆየት እና ትላንትን በማስታወስ የወቅቱን ሥልጣኔ ለዓለም እየመሰከረ ዛሬ ላይ ደርሷል።
ዓመታዊ የጥምቀት በዓልን በጎንደር ለመታደምም ከመላው ኢትዮጵያ እና ከሌሎች የዓለም ሀገራት ጎብኝዎች ይጎርፋሉ። እንግዳ ተቀባዩ የጎንደር ሕዝብም ከበዓሉ ቀደም ባሉት ጊዜዎች የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችን ያደርጋሉ።
ዘንድሮም መጪውን የጥምቀት በዓል በድምቀት እና በልዩ ሁኔታ ለማክበር ጎንደር ሽርጉድ እያለች ነው።
በጎንደር ከተማ የሚገኘው የኤጅ ሆቴል ሥራ አስኪያጅ ደሳለኝ ይልማ ኤጅ ለ2018 ዓ.ም ለጥምቀት በዓልም እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ጥሩ ዝግጅት እንዳለ ነግሮናል።
በጎንደር ከተማ አስጎብኝ ማኅበር ውስጥ ለረጅም ዓመታት እንግዶችን በማስጎብኘት ሥራ ላይ እንደተሠማራ የነገረን ብርሃኑ አበበ ደግሞ በመጪው 2018 ዓ.ም የጥምቀት በዓል ጎንደር እና አካበቢው ላይ ያሉ ታሪካዊ ቦታዎችን ለማሳየት እና ለእንግዶች ታሪክን ሳይዛባ ለመንገር ቀድሜ እየተዘጋጀሁ ነው ብሎናል።
የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ማርያም ካሳሁን የ2018 ዓ.ም የጥምቀት በዓል ከመከበሩ በፊት ያሉት ሳምንታት 16ኛው የባሕል ሳምንት በጎንደር በሚል ንቅናቄ እቅዶች ታቅደው የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነ ተናግረዋል።
የበዓል ሳምንቱ ከዚህ በፊት የአጼ ቴዎድሮስ የልደት በዓል ከሚከበርበት ጥር 06 ጀምሮ ሲከበር እንደነበር ያስታወሱት ኀላፊዋ በዚህ ዓመት ደግሞ በልዩ ሁኔታ ከጥር 01 ጀምሮ እስከ ጥር 09/2018 ዓ.ም ድረስ እንደሚቀጥል ነው የገለጹት።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ጉዳዮች ቱሪዝሙ ተጎድቶ መቆየቱን የተናገሩት ኀላፊዋ ተጠሪነቱ ለጎንደር ከተማ ከንቲባ የኾነ አንድ ዐቢይ እና ስምንት ንዑስ ኮሚቴዎች ተዋቅረው ወደ ሥራ መገባቱን ነው የገለጹት።
በዚህ ዓመት እንደ ጎንደር ከተማ “ኢትዮጵያን በጎንደር እናግኝ” በሚል መሪ መልዕክት መጪው የጥምቀት በዓልን በልዩ ሁኔታ ለማክበር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ ነውም ብለዋል። የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ የሚያረዝም እንዲኾን በቅንጅት እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የጎንደር ታሪክ ሰፊ ነው፤ የቤተ መንግሥቱ እድሳት እና የኮሪደር ልማት ሥራዎች ደግሞ ጎንደርን የበለጠ አድምቀዋታል ብለውናል።
ጎንደር አሁን ላይ ከስጋት ነጻ ኾና 24 ሰዓት ለጎብኝዎች እና ለሥራ ምቹ ናት ብለውናል። የጎንደር ሕዝብ እንግዶችን ለመቀበል ሽር ጉድ እያሉ እንደኾነም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያውያን ጥምቀትን በጎንደር እንዲታደሙ እና የአካባቢውን ባሕል፣ ወግ እና ትውፊት እንዲጋሩ የእነሱንም እንዲያካፍሉ ኑ ጥምቀትን በጋራ እናክብር ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!









