ባሕርዳር: ታኅሣሥ 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢየሱስ ክርስቶስ እና የቅዱስ ወንጉስ ላሊበላ የልደት በዓል በየዓመቱ ታኀሣሥ 29/በሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም በድምቀት ይከበራል፡፡
ይህን በዓል ከሌሎች አካባቢዎች የተለየ የሚያደርገው የቤዛ ኩሉ ሥነ ሥርዓቱ መኾኑን የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም ዋና አሥተዳዳሪ አባ ህርያቆስ ፀጋዬ አስረድተዋል፡፡
ይህ ሥነ ሥርዓት በቤተክርስቲያኒቷ ሕግ አገልግሎቱ እና ቀኖናው አንድ ኾኖ በተለይ በቀሳውስቱ የሚካሄደው የቤዛ ኩሉ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ግን ከሌሎች እንደሚለይ እና ብዙዎች ሊያዩት የሚጓጉለት አስደናቂ ኹነት መኾኑን ነው የተናገሩት፡፡
የቤዛ ኩሉ ሃማኖታዊ ሥርዓት በዋዜማው ምሽት ጀምሮ እንደሚካሄድም ነው የገለጹት፡፡ ቤዛ ኩሉ በቀሳውስት ዝማሜ፣ በአማኞች እልልታ እና በተለያዩ ደማቅ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ታጅቦ ነው የሚካሄደው፡፡
ይህንን በዓል ለማክበር የሚመጡ እንግዶችን በመቀበል የአካባቢው ማኅበረሰብ ከጥንት አባቶቹ የወረሰው ድንቅ መንፈሳዊ ትውፊት እንዳለም ነው ያወሱት።
በዚህም ለእንግዶች ያላቸውን የማካፈል፣ ለእንግዶች ክብር መስጠት፣ በቤተክርስቲያን የተለያዩ ተሳትፎዎችን በማድረግ በዓሉ በድምቀት እንዲከበር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም ነው ያብራሩት፡፡
ለዚህም የቅድመ ዝግጅት ሥራው ተጠናቆ የሚመጡ እንግዶችን በመጠባበቅ ላይ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡
በሁሉም አቅጣጫ ያሉ አማኞች እና የበዓሉ ታዳሚዎች በዚህ ድንቅ መንፈሳዊ ቦታ ላይ በመገኘት የበረከቱ ተሳታፊ እንዲኾኑ መንፈሳዊ ጥሪያቸውንም አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፦ሰናይት በየነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!









