ላሊበላን የሚጎበኙ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።

0
61
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 23/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የቱሪዝም ዘርፉ የላሊበላ ከተማ ዋነኛ የምጣኔ ሃብት መሠረቷ ነው። በሰላሙ ጊዜ በዓመት ከ40 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች አካባቢውን ይጎበኙ እንደነበር የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር የባሕል ቱሪዝም ስፖርት ጽሕፈት ቤት መረጃ ያሳያል።
ይሁን እንጅ በኮሮና፣ በሰሜኑ ጦርነት እና ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ በክልሉ በተከሰተው ግጭት ዘርፉ መጎዳቱን አሚኮ ያነጋገራቸው የመስተንግዶ ተቋማት ባለቤቶች እና ባለሙያዎች ነግረውናል።
የሂልቶፕ ሎጅ ሥራ አሥኪያጅ ብርሃነመስቀል ይማም እንዳሉት የቱሪዝም ዘርፉ በኮሮና ወረርሽኝ እና በተከታታይ በተከሰተው ግጭት የሆቴሎች ሥራ ተቀዛቅዞ ቆይተዋል፤ ሌሎች በዘርፉ በቀጥታ ተሠማርተው የነበሩ ሁሉ ቀጥተኛ ተጎጅ መኾናቸውንም አንስተዋል።
በ2018 ዓ.ም መጀመሪያ ጀምሮ ግን ዘርፉ መነቃቃት ማሳየቱን ነው የገለጹት። አሁን ላይ ሆቴሉ ያሉት አልጋዎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ አገልግሎት በመስጠት ላይ መኾናቸውን ገልጸውልናል።
የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ በሚያራዝም መንገድ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል። የላሊበላ ከተማ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዲያቆን አዲሴ ደምሴ እንዳሉት በሰላሙ ጊዜ በዓመት ከ40 ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች አካባቢውን ይጎበኙ እንደነበር አንስተዋል።
ይሁን እንጅ ከሰሜኑ ጦርነት በኋላ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ቁጥር እስከ 776 ደርሶ እንደነበር ገልጸዋል። በችግሩ ምክንያት ሆቴሎች ሥራ በማቆማቸው ከ1ሺህ 500 በላይ ቋሚ ሠራተኞችም ከሥራ ውጭ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ይሁን እንጅ በ2018 በጀት ዓመት በተፈጠረው አንጻራዊ ሰላም እስከ ትኅሣሥ 22/2018 ዓ.ም 4ሺህ 818 የውጭ ሀገር ዜጎች አካባቢውን ጎብኝተዋል።
ከዚህም በባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ስሌት መሠረት ከ31 ሚሊዮን ብር በላይ በከተማው የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ መከናወኑን ነው የገለጹት።
ከታኅሣሥ 1/2018 ዓ.ም እስከ ታኅሣሥ 22/2018 ዓ.ም ባለው ጊዜ ብቻ ከ1ሺህ በላይ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች ወደ ከተማዋ መግባታቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here