ኢራንቡቲ – ሌላዋ የጥምቀት ሙሽራ!

0
82


ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ‎‌በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት በአደባባይ ከሚከበሩ ክብረ በዓላት መካከል የጥምቀት በዓል አንዱ ነው፡፡ በዓሉ በዩኔስኮ የማይዳሰስ ባሕላዊ ቅርስ ኾኖ በ2012 ዓ.ም ተመዝግቧል። በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች በድምቀት የሚከበር ሲኾን በሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ የሚከበረው የኢራንቡቲ ጥምቀት ደግሞ አንዱ መገለጫ ነው።

‎‌በዚህ ዓመት በዓሉን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እያደረጉ መኾኑን የነገሩን የሸንኮራ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ገዳም አሥተዳዳሪ መጋቢ ሐዲስ መልአከ መንክራት ቆሞስ አባ አብርሃም ዳኛቸው ናቸው፡፡ ለጥምቀት በዓል መከበር ታሪካዊ መነሻው የኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ መጠመቅ ነው፡፡ ጥምቀት የሰው ልጆችን ከኃጢያት ባርነት ያስወጣ እና ሀብተ ጸጋ እና መንፈስ ቅዱስ ያስገኘ ነው ብለዋል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ በመጠመቅ ትህትናን ያስተማረበት በመኾኑ ጥምቀት አንድነትን፣ ሰላምን፣ ፍቅርን እና መታዘዝ የሚሰበክበት ሃይማኖታዊ ሥርዓት ነው በማለት ገልጸውታል፡፡

‎ጥምቀት በምንጃር ሸንኮራ ኢራንቡቲ ልዩ የሚያደርገው ለ624 ዓመታት የአባቶችን ታሪክ፣ ባሕል፣ ትውፊት በመጠበቅ አንድነቱን እና ፍቅሩን በመስበክ በኅብረት ሲከበር የቆየ መኾኑን አንስተዋል፡፡ ከ18 አብያተ ክርስቲያናት 44 ታቦታት ወደ ባሕረ ጥምቀቱ ወርደው በአንድነት ሳይለያዩ የሚያከብሩት በዓል ነው ይላሉ፡፡ ታቦታቱ የሚወርዱበት እንደ ኢየሩሳሌም ዮርዳኖስ ወንዝ ወደ ምሥራቅ የሚፈስሰው የሸንኮራ ወንዝ ለበዓሉ የተለየ ድምቀት እንደሰጠው ይናገራሉ፡፡

‎በቦታው ምዕመናን ድኅነተ ሥጋ እና ድኅነተ ነፍስ የሚያገኙበት ነው ብለዋል፡፡ አብያተ ክርስቲያናት በየዓመቱ በየተራ አሳዳሪ ይኾናሉ ያሉት አሥተዳዳሪው ዘንድሮ ሸንኮራ ዮሐንስ ተረኛ በመኾኑ የአሳዳሪነቱን ሚና ለመወጣት በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡

‎ታቦታቱ በተለያየ ርቀት ላይ የሚገኙ እና ወጣ ገባ በኾነ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ከሁለት እስከ ሦስት ሰዓታትን ተጉዘው በመውረድ የሚያከብሩት መኾኑን ነው የገለጹት፡፡ ከወረዳው ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ጋር በጋራ የአካባቢውን ባሕል በጠበቀ መልኩ እንዲከበር እየሠሩ መኾኑን እና ዘንድሮ ለ624ኛ ጊዜ ይከበራል ነው ያሉት፡፡

‎የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ቤተ ክህነት ኀላፊ ሊቀ ካህናት ሞገስ ተፈራ በበኩላቸው በዓሉን በድምቀት ለማክበር ከተረኛ አሳዳሪው ቤተ ክርስቲያን ጋር በጋራ ያሬዳዊ ዝማሬ የሚያቀርቡ የሃይማኖት አባቶች ሁነቱን ለማድመቅ ተዘጋጅተዋል ብለዋል፡፡

‎የቦታውን ጽዳት በመጠበቅ፣ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ ትውፊቱን በሚመጥን መልኩ በድምቀት ለማክበር መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

‎የጥምቀት በዓል ከዋዜማው ጥር 10 ጀምሮ እስከ ጥር 12 የሚቆይ ሲኾን ቤተ ክርስቲያኗ በራሷ ትውፊት በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ምዕመናን የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

‎የኢራንቡቲ ነዋሪው አቶ ኃይሉ ገድሌ የጥምቀት በዓል በኢራንቡቲ ከአዲስ አበባ እና ከሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎችም በርካታ ምዕመናን ተሰባስበው በድምቀት የሚያከብሩት እንደኾነ ገልጸውልናል፡፡ ለበዓሉ ማኅበረሰቡ ከሃይማኖት አባቶች ጋር በትብብር በቂ ዝግጅት እያደረጉ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

‎የምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አስናቀች በቀለ ጥምቀትን በኢራንቡቲ በደመቀ ኹኔታ ለማክበር ከማኅበረሰቡ እና ከቤተ ክርስቲያኗ ጋር የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ሃይማኖታዊ እና ባሕላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር ለማድረግ ውይይት ተካሂዷልም ነው ያሉት፡፡

‎የሰሜን ሸዋ ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ ተዋበች ጌታቸው በዓሉን በድምቀት ለማክበር እንደዞን አስፈላጊው ድጋፍ እና ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይም አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ እንዲኾን የማስተዋወቅ ሥራዎች እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

‎ዘጋቢ፡- ፍሬሕይወት አዘዘው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here