ገንዳ ውኃ: ታኅሣሥ 25/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የምዕራብ ጎንደር ዞን ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ 17ኛውን ዞን አቀፍ የባሕል እና ኪነ ጥበብ ፌስቲቫል “አብሮነት በነጭ ወርቅ ምድር” በሚል መሪ መልዕክት አክብሯል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ ኀላፊ ይግለጥ አበበው ቱሪዝም ለሀገር ግንባታ እና ዕድገት መሠረት በመኾኑ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን ማልማት እና ማስፋት ያስፈልጋል ብለዋል።
የአካባቢውን ባሕል ለማስተዋወቅ የባሕል ፌስቲቫል ትልቅ ድርሻ እንዳለውም ገልጸዋል።
በኪነ ጥበብ ዘርፉ ወጣቶችን በማሳደግ የሀገርን ባሕል እንዲያስተዋውቁ እና እንዲጠብቁ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።
ኪነ ጥበብ ለአንድ ሀገር ዕድገት ከፍተኛ ሚና ያለው በመኾኑ በዞኑ እየተከበረ ያለውን የባሕል ፌስቲባል አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ አስያ ዑመር የባሕል ፊስቲቫሉ ዓላማው ተተኪ የጥበብ ሰዎችን ለማፍራት ታስቦ የተዘጋጀ መኾኑን አብራርተዋል።
የአካባቢውን ባሕል በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ በቲያትር፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በውዝዋዜ እና በሌሎች ኹነቶች ትኩረት ተደርጎ ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።
ኪነ ጥበብ ሰላምን፣ አንድነትን እና አብሮነትን ለማጠናከር ድርሻው ከፍተኛ መኾኑንም ገልጸዋል። የባሕል ፌስቲቫሉ የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም ዙርፍ ለማነቃቃት የሚያስችል እንደኾነም ጠቁመዋል።
በዞኑ ያሉትን የቱሪዝም ዘርፎች ለማስተዋወቅ ጥረት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
የበዓሉ ተሳታፊዎችም የአካባቢያቸውን ባሕል ለሌላው አካባቢ ለማስተዋወቅ ዕድሉን ስላገኙ ደስተኛ መኾናቸውን ተናግረዋል። በዓሉን ከማክበር ባለፈ አንድነታቸውን እና ፍቅራቸውን እንደሚያጠናክረውም ገልጸዋል።
የዛሬው የባሕል ፌስቲቫል በኪነ ጥበብ ዘርፉ ትልቅ መነቃቃትን የፈጠረ መኾኑን አንስተዋል። ቀጣይም ባሕላቸውን ለማስተዋወቅ እንደሚሠሩም ነው የተናገሩት።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!









