ኢየሩሳሌምን በደብረ ሮሃ

0
75
ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያ የኪነ ሕንጻ ጥበብ አብቦ ከወጣባቸው ዘመናት ውስጥ የዛግዌ ሥርዎ መንግሥት አንዱ ነው።
የወቅቱ ነጉሠ ነገሥታት በአክሱም ዘመነ መንግሥት የታየውን የኪነ ሕንጻ ጥበብ አጠናክረው እንዳስቀጠሉት የሃይማኖት አባቶች ይናገራሉ።
ቅዱስ ላሊበላ፣ ቅዱስ ገብረ ማርያም፣ ቅዱስ ነአኩቶለአብ እና ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ የራሳቸው የኪነ ሕንጻ መታሰቢያ አስቀምጠው ካለፉት ውስጥ ግንባር ቀደሞቹ ናቸው።
የደብረ ሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም የስብከተ ወንጌል አገልጋይ ቀሲስ ይሔነው መልኩ ቅዱስ ላሊበላ መንፈሳዊ ራዕይ ተገልጦለት በአስርቱ ትዕዛዛት ምሳሌ አስር አብያተ ክርስቲያናትን በደብረ ሮሃ እንዳሠሩ ገልጸዋል።
ቅዱስ ገብርኤል እና ቅዱስ ሩፋኤል በአንድ ቤተ ክርስቲያን በሁለት ቤተ መቅደስ ውስጥ ስለሚገኙ አብያተ ክርስቲያናቱ አስራ አንድ ተደርገው እንደሚወሰድ ገልጸዋል። ቤተ መቅደሶችን ለማነጽ ደግሞ 23 ዓመታት እንደፈጀ ተናግረዋል፡፡
የአብያተ ክርስቲያናቱ ኪነ ሕንጻ በምድራዊት ኢየሩሳሌም እና በሰማያዊት ኢየሩሳሌም ምሳሌ የተገነቡ ናቸው። በምድራዊ ኢየሩሳሌም የሚመሰሉት በምድብ አንድ የሚገኙት እና በመጀመሪያ የታነጹ ናቸው።
እነዚህም ቤተ ማርያም፣ ቤተ መድኃኔዓለም፣ ቤተ ጎልጎታ (ቤተ ሚካኤል)፣ ቤተ መስቀል እና ቤተ ደናግልን ያጠቃልላል።
ቅዱስ ላሊበላ ምድራዊ ኢየሩሳሌምን በደብረ ሮሃ ተክቶ ሲገነባ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሔድ ሁኔታዎች ያልፈቀዱላቸው አማኞች መንፈሳዊ ሥርዓታቸውን እንዲፈጽሙም በማሰብ መኾኑንም ገልጸውልናል።
ምድራዊ ኢየሩሳሌም ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ተዓምር የፈጸመባቸው እንደ ቀራኒዮ፣ ቤተልሄም፣ ዮርዳኖስ፣ ቃና ዘገሊላ፣ ደብረ ታቦር ተራራ፣ ደብረ ዘይት፣ ቢታኒያ፣ በመሳሰሉ በኢየሩሳሌም ውስጥ የሚገኙ ቦታዎች ምሳሌ የተገነቡ መኾናቸውንም ቀሲስ ይሔነው ገልጸውልናል።
በሰማያዊት ኢየሩሳሌም የሚመሰሉት ደግሞ በምድብ ሁለት የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናትን ያካትታል። ቤተ ገብርኤል፣ ቤተ አማኑኤል፣ ቤተ መርቆርዮስ፣ ቤተ አባ ሊባኖስ ይገኙበታል። አራቱም በአንድ አቅጣጫ ይገኛሉ።
ይህ ምድብ አሠራሩ ሰማያዊ ባሕርይ የተላበሰ፣ የመላዕክት መቀመጫ ቦታ፣ የሲኦል እና ገሃነመ እሳት፣ የገነት እና መንግሥተ ሰማያት ምሳሌን የያዘ ነው።
እንዲሁም አንዳንዶች በምድብ ሦስት ለብቻው የሚገኘው እና በኖኅ መርከብ ምሳሌ ተደርጎ የታነጸው የቅዱስ ላሊበላ የመጨረሻ ሥራ ቤተ ጊዮርጊስ እንደኾነ ይናገራሉ። ቤተ ጊዮርጊስ የአራቱ አቅጣጫዎች አመላካች ኖሮት በመስቀለኛ ቅርጽ የታነጸ ቤተ መቅደስ ነው፡፡
ቅዱሱ ንጉሥ አብያተ ክርስቲያናቱን ሲያንጹ እንደ አሁኑ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ሳይኾን በመጥረቢያ፣ መሮ፣ መዶሻ በመሳሰሉ መሳሪያዎች እንደነበርም ገልጸዋል።
የአብያተ ክርስቲያናቱ ኪነ ሕንጻ ሥራዎችም እንደ ዘመኑ ግንባታዎች ከታች ወይንም ከመሠረቱ ወደ ላይ ሳይኾን ከላይ ከጣሪያው ወደ ወደ ታች የተሠራ መኾኑ ልዩ ያደርገዋል።
ቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናቱን ሲያንጽ መንገዶችን እና የውኃ መፋሰሻዎችን ጭምር ታሳቢ አድርጎም ነው።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here