ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 26/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በባሕር ዳር ከተማ የሚገኘው የሰለሞን መንደር የባሕል ሕክምና እና የምርምር ማዕከል የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ምክንያት በማድረግ ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ አደረጓል።
ማዕከሉ 267 ለሚኾኑ በባሕር ዳር ላሉ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው አቅመ ደካሞች ዶሮ፣ ዘይት እና ሽንኩርት እንዲሁም 89 ለመኾኑ በመሸንቲ አካባቢ ለሚኖሩ ሰዎች ለልደት በዓል መዋያ የሚኾን ለእያንዳንዳቸው 2 ሺህ ብር ድጋፍ አድርጓል።
በአጠቃላይ ማዕከሉ ለዚህ ድጋፍ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ ማድረጉ ነው የተገለጸው።
ድጋፍ ማድረግ በፈጣሪም የተወደደ ተግባር ነው ያሉት የማዕከሉ መሥራች መምህር ክንፈ ሩፋኤል ፋንታሁን (ዶ.ር) ከዚህ በፊትም ለተከታታይ ዓመታት በተለያዩ በዓላት ወቅት ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ማዕከሉ ድጋፍ ሲያደርግ ተረጅዎችን ደካማ አድርጎ በማሰብ ሳይኾን እህት እና ወንድም ነን ብሎ በማሰብ ነው ብለዋል።
በየአካባቢው ያለው ለሌለው በማካፈል ሁሉም ተደስቶ በዓልን እንዲያሳልፍ ማገዝ ያስፈልጋልም ነው ያሉት።
ድጋፍ የተደረገላቸው ወይዘሮ ማህሌት አለኸኝ ባለፉት ዓመታት በዓላትን ለማክበር ይቸገሩ እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁንም ለልጆቼ ምንድን ነው የማቀምሳቸው ብየ ሳስብ ነበር፤ ዛሬ ከበዓሉ ቀን ቀደም ብሎ የተደረገላቸው ድጋፍ ሀሳባቸውን እንዳቀለላቸው እና በዓሉንም በደስታ እንደሚያሳልፉ ተናግረዋል። ስለተደረገላቸው ድጋፍም ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።
ሌላው ድጋፍ የተደረገላቸው ደግሞ አቶ ደሴ ጋረድ ይባላሉ። በጤና ጉድለት ምክንያት መሥራት ስለማይችሉ ኑሮን ማሸነፍ ከባድ እንደኾነባቸው ተናግረዋል።
በፊት በዓል ሲመጣ ለልጆቻቸው የሚያቀርቡት ያስጨንቃቸው እንደነበር የገለጹት አቶ ደሴ ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ ለበዓል መዋያ ከሰለሞን መንደር የበዓል ማዕከል ድጋፍ እንደሚደረግላቸውም ተናግረዋል።
በዚህም በዓሉን ከቤተሰቦቻቸው ጋር በደስታ እንደሚያሳልፉ ነው የጠቆሙት። ለረጅ ማዕከሉም ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።
የባሕር ዳር ከተማ ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ሰብለ ዘውዱ የሰለሞን መንደር የባሕል ማዕከል በብዙ ውጣ ውረድ ኾነው ገንዘባቸውን ሳይሰስቱ በተለያዩ በዓላት ወቅት ደካሞችን በመደገፍ ለሌሎች ወገኖቻችን አርዓያ በመኾን እያስተማረ ያለ ማዕከል ነው ብለዋል።
ከዚህ በጎ ምግባር ሁላችንም ተምረን የበኩላችንን ድርሻ በመወጣት ወገኖቻችንን ከተረጅነት ወደ አምራችነት ማሸጋገር ይገባል ብለዋል።
ዘጋቢ:-ሰናይት በየነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!









