ባሕር ዳር: ታኅሣሥ 29/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በላሊበላ በድምቀት እየተከበረ ነው፡፡
በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ የኢየሱስ ክርስቶስ የልድት በዓል በታላቅ ድምቀት የሚከበር ሃይማኖታዊ በዓል መኾኑን ገልጸዋል፡፡
በክርስቶስ መወለድ ሰው እና መላዕክት በጋራ ዘምረዋል፤ እረኞች በበረት ተገኝተው የተወለደው የዓለም ጌታ፣ የዓለም መድኃኒት መኾኑን መስክረዋል፤ በዓሉ ፍጹም መንፈሳዊነት ያለው፤ ተጣልተው የነበሩ የታረቁበት፣ ፍቅር የተሰበከበት፣ እንድነት የታወጀበት፣ የፍቅር እና የነጻነት በዓል ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በቱሪዝም እንዱስትሪ ሁሉን አቀፍ ባሕላዊ፣ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ሃብቶች ያሏት መኾኗን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በርካታ ቅርሶችን በዩኔስኮ ያስመዘገበች በአፍሪካ ቀዳሚ ሀገር መኾኗንም ጠቅሰዋል፡፡ የአማራ ክልል በቱሪዝም ሃብት የታደለ መኾኑንም እንስተዋል፡፡
የቅዱስ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በዘመኑ ዓለም ቴክኖሎጂ ሊሠሩ እና ሊደገሙ ብቻ አይደለም ሊታሰቡ አይችሉም ነው ያሉት፡፡ የዓለም ሕዝብ በስስት የሚጎበኛቸው፣ ዩኔስኮ ድንቅነታቸውን የመሰከረላቸው ቅርሶች ናቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለዓለም ካበረከተቻቸው ዘመን አይሽሬ የሥልጣኔ ትሩፋቶች መካከል ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚመደቡ ናቸው ነው ያሉት።
ቅርሶቹ ታላቅ ነበርን ስንል ሕያው ምስክሮቻችን፣ ታላቅም እንኾናለን ስንል የቁጩት እና የይቻላል መንፈስ ምንጮቻችን፣ ኢትዮጵያዊነታችን ስናስብ መታሰሪያችን ኾነው እያገለገሉ ያሉ ናቸው ብለዋል።
ሕዝብ ከፈጣረው ጋር የሚገናኝባቸው፣ ጸሎቱን የሚያደርስባቸው ቅዱስ ቅርሶች ናቸው ብለዋል። በዓለም የቱሪዝም ገበያ የሀገራችን መለያዎች እና አውራ የቱሪዝም መዳረሻዎች እንደኾኑም ነው የገለጹት።
በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም እሳቤ ለቱሪዝም ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት መስፋፋቱን እና ኢትዮጵያን የሚጎበኙ ጎብኝዎች ቁጥር መጨመሩንም ገልጸዋል።
የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ለመጠገን እየተሠራ ምኾኑን ነው የተናገሩት። በዓላትን መጠበቅ፣ ማክበር እና ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባም ለመላክተዋል፡፡
በዓላት የሕዝብን ግኙነት በጽኑ መሠረት ላይ እንዲቆም በሚያደርጉ መልኩ ማክበር እንደሚገባ ገልጸዋል። በዓሉ የደስታ እና የበረከት እንዲኾንም ተመኝተዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!









