ጥር ወር ለባሕር ዳር ከተማ ልዩ ነው።

0
57
ባሕር ዳር፡ ጥር 05/2018ዓ.ም (አሚኮ) በጥር ወር ሃይማኖታዊ በዓላት እና ባሕላዊ ሁነቶች በደመቀ ሁኔታ ከሚከበሩባቸው ከተሞች መካከል ባሕር ዳር ከተማ አንዷ ናት።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደርም የውጭ እና የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች በእነዚህ በዓላት እና ሁነቶች እንዲታደሙ እየሠራ ነው። ጥርን በባሕር ዳር” በሚል መርሐ ግብር በልዩ ሁኔታ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል።
የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች እና ጎብኝዎችም የጥርን ወር በጉጉት ይጠብቋታል።
ትውልድ እና እድገቱ በባሕር ዳር ከተማ የኾነው መልካሙ ግዛቸው ከ20 ዓመታት በላይ ታንኳ የመቅዘፍ ልምድ እንዳለው ነግሮናል። ቀደም ሲል ባሕር ዳር ላይ በጥር ወር በተደረጉ ሁሉም የታንኳ ውድድሮች ላይ ተሳታፊ እንደነበረም ገልጿል።
በዚህ ዓመት የሚደረገውን የታንኳ ውድድር በጉጉት እየጠበቀ መኾኑንም አንስቷል። ለዘንድሮው ታንኳ ውድድርም ጧት እና ምሽት ላይ ልምምድ እያደረግሁ ነው ብሎናል። በውድድሩ እስከ ሦስተኛ ደረጃ ለመውጣት አስቢያለሁ ነው ያለው።
የባሕር ዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ዋና ጸሐፊ መጋቢ ሥርዓት ሞገስ አንዳርጌ የሰባር ጊዮርጊስ በዓልን በባሕር ዳር በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ከከተማ አሥተዳደሩ ጋር በመቀናጀት ዓብይ እና ንዑስ ኮሚቴዎች ተዋቅረው የቅድመ ዝግጅት ተግባራት እየተሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል።
ከዋዜማው ጀምሮም የተለያዩ ሁነቶች ይኖራሉ፤ ባሕር ዳርን ሊያስጠራ የሚችል በዓል ለማክበር ታስቧል ነው ያሉት። የብስክሌት፣ የታንኳ እና ጀልባ ሽርሽሮች ተለምደው የቆዩ እንደኾኑም ተናግረዋል። በዚህ ዓመት ቅዱስ ጊዮርጊስ ፈረሰኛ ስለኾነ በዓሉን የበለጠ ድምቀት ለመስጠት የፈረስ ትርኢት እንዲኖር ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል።
በሀገር ውስጥ የሚገኙ እና ከሀገር ውጭ ያሉ የባሕር ዳር እና አካባቢው ተወላጆች የቤተክርስቲያንን ክብር መጠበቅ ፤ ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ማገዝ አለብን በሚል ከካቴድራሉ ጋር እየመከሩ እና እየሠሩ መኾናቸውን አንስተዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የጥርን በባሕር ዳር ዝግጅት ዓብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አስሜ ብርሌ ጥርን በባሕር ዳር በድምቀት ለማክበር የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ተናግረዋል፡፡
የጥርን በባሕር ዳር ዝግጅት በባሕል እና ኪነ ጥበብ ፌስቲባል ጥር 01/2018 እንደጀመረ ገልጸዋል። ዝግጅቱ በተለያዩ ሁነቶች ደምቆ እስከ ጥር 30/2018 ዓ.ም ድረስ ይቀጥላል ነው ያሉት። ጥር 30 የቁንጅና ውድድር ተካሂዶ በፓናል ውይይት ይጠናቀቃል ብለዋል።
ከጥርን በባሕር ዳር ፌስቲቫሎች መካከል የብስክሌት እና የታንኳ ሽርሽር፣ ጥር 18 የሚከበረዉ የሰባር ጊዮርጊስ ሃይማኖታዊ በዓል የጥርን በባሕር ዳር ልዩ ድምቀቶች መኾናቸውን አንስተዋል፡፡
በጥር ወር የማጠቃለያ ፕሮግራሙን ጨምሮ 22 ሁነቶች በቀናት ተከፋፍለው እየተከናወኑ ነው ብለዋል። “ጥር ወር ለባሕር ዳር ከተማ ልዩ ነው” ብለዋል።
የዘንድሮውን ጥርን በባሕር ዳር መርሐ ግብር የባሕር ዳር ውበት የበለጠ የተገለጠበት የኮሪደር ልማት ሥራ የተሠራበት፤ የጥርን በባሕር ዳር አካል ለኾነው የብስክሌት ሽርሽር ራሱን የቻለ ምቹ መንገድ የተፈጠረበት በመኾኑ ከቀደሙ ዓመታት ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።
ጣናነሽ ቁጥር ሁለት ወደ ባሕር ዳር ከተማ የመጣችበት እና ሥራ የጀመረችበት፤ ከተማዋ ወደ ሙሉ ሰላም የተሸጋገረችበት ወቅት መኾኑም ልዩ እንደሚያደርገው ጠቅሰዋል።
እያደገች እና እየተዋበች ባለችው የሰላም ከተማ ኑ ጥርን በባሕር ዳር አሳልፉ ብለዋል በመልዕክታቸው።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here