ጣናን ለቱሪስት ዕይታ በስምንት ቦታ ላይ መክፈት ተችሏል፡፡

0
51
ባሕር ዳር: ጥር 06/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ባለዘንባባዋ ከተማ ባሕር ዳር እስካሁን ያላትን ጸጋ ሳትጠቀምበት ቆይታለች፡፡ ከተማዋ አሁን ላይ ግን ያሏትን ጸጋዎች ለማውጣት ጥረት እያደረገች ነው የምትገኘው፡፡
ባሕርዳር ከተማ ውበቷን ከሚያጎሉ ነገሮች ውስጥ ከዘንባባዋ በተጨማሪ የጣና ሐይቅ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡
ጣናን ለጎብኝዎች ምቹ ከማድረግ በተጨማሪ በዩኒስኮ ለማመዝገብ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉንም የክልሉ ባሕል ቱሪዝም ቢሮ ገልጿል፡፡
ይህን ውብ እና የቱሪስት መዳረሻ በዚህ ዓመት በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ነው ጥረት እየተደረገ ያለው፡፡
በዚህ ዓመት በ48ኛው የዩኒስኮ ጉባኤ ላይ እንደሚመዘገብ የገለጸው ቢሮው ለዚህም የዩኒስኮ ሰዎች ወደ አካባቢው መጥተው እንዲያዩ እንደሚደረግ ነው የተጠቆመው፡፡
ከቅድመዝግጅት አኳያም ከጣና ገዳማት አሥተዳዳሪ የሃይማኖት አባቶች ጋር ውይይት ሲካሄድ ስለመቆየቱም ተብራርቷል፡፡
ጣናን በማልማት የውኃ ስፖርት ቱሪዝምን ለመፍጠር ጥረት መደረጉም ተጠቁሟል፡፡ በተለይም በጣና ላይ ያሉ ታንኳዎች የትኛውም ዓለም ላይ ለሚመጡ አዲስ ቱሪስቶች አዲስ እንደኾኑ ገልጿል፡፡
ይህንንም ከዘመናዊው የቱሪዝም ስልት ከጀልባዎች ጋር በማጣመር የታንኳ ቀዘፋ ውድድር በማዘጋጀት የባሕር ዳር ልዩ መለያ ለማድረግ እየተሠራ እንደኾነም ነው የተብራራው፡፡
በጣና ላይ ቱሪስቶች አሳ ማጥመድ እና መዝናናት የሚችሉበት ሁኔታ ለመፍጠርም በጣና ላይ ልማት እየተሠራ እንደኾነም ቢሮው አስገንዝቧል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here