ጋዲሎ ሜዳ – ሌላው የ44 ታቦታት መውረጃ የጥምቀት ጌጥ

0
51

 

ደብረ ብርሃን፡ ጥር 08/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአንድ ቦታ 44 ታቦታት ይወርዱበት የነበረው እና በኤፍራታና ግድም ወረዳ የሚገኘው ጋዲሎ ሜዳ ጥምቀት በድምቀት ከሚከበርባቸው የሰሜን ሸዋ ዞን አካባቢዎች ውስጥ አንዱ ነው።

በቀደምት ጊዜያት ዓይነቱ ለየት ያለና በአንድ ቦታ 44 ታቦታት ተሰባስበው የሚወጡበት፣ ረጅም ታሪክ ያለው ሃይማኖታዊ ስፍራ ነው ጋዲሎ ሜዳ፡፡

ይሄን ሥርዓት በተሟላ መንገድ ለመመለስ እና እንደቀድሞው በዓሉ በድምቀት የሚከበርበትን አግባብ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መኾኑን ከወረዳው ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በዚህ ታሪካዊ የጥምቀት ማክበሪያ ቦታ በዓሉ አሁንም ሃይማኖታዊ አከባበሩን እንደጠበቀ እና በባሕላዊ ጨዋታዎች ደምቆ ይውላል። ከሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቱ ባለፈ የገና ጨዋታ (ሩር)፣ ባሕላዊ ጭፈራ እና አካባቢውን የሚገልጹ ዜማዎች የሁነቱ ድምቀቶች ናቸው።

በዓሉን ለማክበር ሰፊ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ አንደሚገኝ የገለጹልን ደግሞ የወረዳው አሥተዳዳሪ አበራ መኮንን ናቸው። የጥምቀተ ባሕር የመገንባት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ይህ ታሪካዊ ሃይማኖታዊ ስፍራ የጥንት ታሪኩን ጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ትልቅ የቱሪዝም መዳረሻ እተሠራ ነው ብለዋል፡፡ የተለያዩ የመሠረተ ልማት ተግባራት እየተሟሉ መኾናቸውንም ጠቁመዋል።

ጋዲሎ ሜዳ ከአጣዬ ከተማ በ20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ታሪካዊ ቦታ ነው፡፡

ዘጋቢ፦ገንዘብ ታደሰ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here