ባሕር ዳር: ጥር 10/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጣና ሐይቅ ደብረ ማርያም ገዳም በ12ኛው ክፍለ ዘመን በአጼ ይኩኑ አምላክ ዘመነ መንግሥት አቡነ ታዲዮስ በተባሉ አባት እንደተመሠረተች ይነገራል። በጣና ሐይቅ ከሚገኙት ቀደምት ገዳማት መካከልም አንዷ ናት።
የጣና ሐይቅ ደብረ ማርያም ገዳም አሥተዳዳሪ መላዕከ ፀሐይ ቆሞስ አባ ገብረሥላሴ ዓለም እንደገለጹት የጥምቀት በዓል በገዳሟ በተለየ መልኩ ይከበርባታል ብለዋል።
ብዙ ታቦታት ከየብስ ተነስተው ወደ ባሕር ይጓዛሉ፣ ደብረ ማርያም ግን ከባሕር ተነስታ ወደ የብስ በመጓዝ ጥምቀትን ታከብራለች ነው ያሉት።
በየብስ ታቦታት በፈረስ እንደሚታጀቡ ሁሉ በደብረ ማርያም ጥምቀትም በታንኳ እና በጀልባ መታጀቧ ልዩ እንደሚያደርገው አስረድተዋል። በተለይም ታቦተ ሕጉ ዓባይ እና ጣና በሚለያዩበት “ዓባይ ራስ” በሚባለው አካባቢ ሲያልፍ ጣና ሐይቅን እና ዓባይን እየባረከ ይጓዛል ነው ያሉት።
ገዳሟ ለበዓሉ ከ20 በላይ ጀልባዎችን ትከራያለች፣ በግል ደግሞ አማኞች የግል ጀልባቸውን ይዘው በመምጣት እንደሚያጅቡ ገልጸዋል። ታቦቱ በጀልባ ላይ ኾኖ ምዕመናን ደግሞ በባሕላዊ ጥበበ ከደንገል በተዘጋጀ ታንኳ እና በትናንሽ ጀልባዎች በመኾን በዝማሬ፣ በእልልታ፣ በጭፈራ ታቦታቱን ያጅባሉ ብለዋል።
በኋላም “ጨረጨራ ግድብ” በሚባለው አካባቢ ገዳሟ ባዘጋጀችው ማረፊያ ላይ ሥርዓተ ጥምቀት ታከናውናለች። ይህ የአከባበር ትዕይንት ልዩ ገጽታን ስለሚፈጥር ለጎብኝዎች አይረሴ ትዝታን ይፈጥራል ነው ያሉት።
ወጣት ሳለዓምላክ ፈንታሁን የደብረ ማርያም አካባቢ ነዋሪ ነው። በየዓመቱ የጥምቀት በዓልን በናፍቆት እንደሚጠብቅ አስተያየቱን ለአሚኮ ሰጥቷል። ምክንያቱ ደግሞ ጥምቀት በደብረ ማርያም ልዩ ድባብ እና ትውስታን የሚፈጥር ስለመኾኑ ነው ያጫወተን።
ወጣቱ እንደሚለው ጥምቀት ከመድረሱ በፊት ከጓደኞቹ ጋር በመኾን ደንገል ይቆርጣሉ፣ ያደርቃሉ፣ ቀጥሎም ከቀደምቶቹ አባቶች በተማረው ሀገር በቀል ጥበብ ታንኳ ያዘጋጃሉ።
ከከተራ ጀምሮ ከደንገል ያዘጋጀውን ታንኳ በመጠቀም በልዩ ትርኢት ከጓደኞቹ ጋር ታቦቱን እያጀቡ ጥምቀትን በልዩ ሁኔታ እንደሚያከብሩም ይገልጻል።
ባለ ጀልባ የኾኑት አቶ ብርሃኑ አንተነህ ጥምቀት በደብረ ማርያም ገዳም የተለየ ደስታን ይፈጥራል ብለውናል። በዚህም ምክንያት በየዓመቱ ቀርቼ አላውቅም ይላሉ።
አከባበሩ አይረሴ ትዝታን የሚፈጥር ስለመኾኑም ተናግረዋል። ጥምቀትን በደብረ ማርያም ያየ ሌላ ጊዜ አይቀርም ይላሉ። ቱሪስቶችም ከሌላው አካባቢ የተለየ ኾኖ ስለሚያገኙት እንደሚደሰቱበት ገልጸዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!









