የታንኳ ቀዘፋ ውድድር የቱሪስቶችን ቆይታ ለማራዘም ሚናው የጎላ ነው።

0
42
ባሕር ዳር: ጥር 14/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የጣና ሐይቅ ደሯ ባለዘንባባ ከተማ በጥር ወር በርካታ ኹነቶችን ታስተናግዳለች። ኹነቶችን ተከትሎም ልዩ ውበት እና ድምቀትን ትጎናጸፋለች። የጎብኝዎችን ቀልብ የምትስብበትም ወቅት ነው።
በከተማዋ እየተከበረ ያለው የ”ጥርን በባሕር ዳር” መርሐ ግብር አካል የኾነው የታንኳ ቀዘፋ ውድድር እና የጀልባ ትርኢት በዛሬው ዕለት በጣና ሐይቅ ተካሂዷል።
ወጣት ኑርልኝ ጌትነት ታንኳን ከደንገል በማዘጋጀት እና ዓሣ በማስገር እየተዳደረ እንደኾነ ገልጾልናል። ዛሬ በታንኳ ውድድሩ ተሳትፎ ሦስተኛ በመውጣቱ መደሰቱን ገልጾልናል።
ውድድሩ በየዓመቱ በጉጉት የሚጠብቀው ስለመኾኑ ተናግሯል። በቀጣይም የሰባሩን ጊዮርጊስን ለማጀብ ዝግጁ መኾኑን ገልጿል።
ሌላኛዋ የውድድሩ ተሳታፊ እና በሴቶች 1ኛ የወጣችው ወጣት መሬም ጥላሁን ውድድሩ ደስታን የሚፈጥር ነው ብላለች። በውድድሩ ስትሳተፍ ለመጀመሪያ ጊዜ መኾኑን ገልጻልናለች።
በታንኳ ሥራ ጨፌን ከጣና ሐይቅ በማውጣት ቤተሰቦቿን እያስተዳደረችበት እንደምትገኝ ተናግራለች። በዛሬው ውድድር ተሳትፋ አንደኛ በመውጣቷ ደስታን እንደፈጠረላት ገልጻለች።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ኀላፊ ጋሻው እንዳለው ባሕር ዳር ከምትታወቅባቸው የባሕል ስፖርቶች መካከል የታንኳ ቀዘፋ አንዱ ነው ብለዋል።
የታንኳ ቀዘፋ ውድድሩ በጣና ሐይቅ ላይ የነበረውን ቀደምት የባሕር ላይ ትራንስፖርት አጉልቶ የሚያሳይ መኾኑን ገልጸዋል። ተወዳዳሪዎችም በታንኳ ቀዘፋ ያላቸውን ልዩ መክሊት ያሳየ ነው ብለዋል። የታንኳ ቀዘፋ ውድድሩ የቱሪስቶችን ቆይታ ለማራዘም ሚናው የጎላ ስለመኾኑም ጠቁመዋል።
ውድድሩ ከጥንት ጀምሮ የነበረ ቢኾንም በተለይም ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት በተነቃቃ መልኩ እየተካሄደ መኾኑን አንስተዋል።
“ጥርን በባሕር ዳር” በባሕል አልባሳት ትዕይንት፣ በኪነ ጥበብ ምሽት፣ በሰባሩ ጊዮርጊስ እና በሌሎችም መርሐ ግብር እስከ ወሩ መጨረሻ ድረስ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here