ባሕር ዳር: ጥር 17/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ባሕር ዳር ከተማ ስትነሳ የጣና ሐይቅ ውበት፣ የዓባይ መነሻነት እና የባሕር ዳር ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ይታወሳሉ።
ይህ ካቴድራል የባሕር ዳር ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ምልክት ነው። ቤተ ክርስቲያኑ ከተመሠረተ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ በከተማዋ ታሪክ፣ ማንነት እና ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ያበረከተው ሚና ከፍተኛ ነው።
ከ1961 ዓ.ም ጀምሮ በባሕር ዳር ከተማ የኖሩት አቶ ይግዛው በለጠ ባሕር ዳር ከተማ ዛሬ ላይ ከመድረሷ በፊት በጣና ሐይቅ ዳርቻ የምትገኝ ትንሽ መንደር ነበረች ይላሉ።
በዚያ ወቅት በመንደሩ አርሶ አደሮች፣ ዓሣ አጥማጆች እና ጥቂት ነዋሪዎች ብቻ የሚኖሩባት ነበረች። የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የሳር ክዳን በነበረበት ጊዜ ጀምሮ እንደሚያስታውሱ ነግረውናል። በዚያም ጊዜ የሰባር አፅሙ ጊዮርጊስ በዓል በታላቅ ድምቀት እንደሚከበርም ያስታውሳሉ።
የቤተ ክርስቲያኑ የወንጌል መምህር ዮሴፍ ዳኛው የአካባቢው ሕዝብ መንፈሳዊ ፍላጎት እና የእምነት ጽኑ ተስፋ ለቤተ ክርስቲያኑ መመስረት መነሻ እንደኾነ ገልጸዋል። ባሕር ዳር ከተማ መኾን የጀመረችውም የቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ከተተከለ በኋላ መኾኑን ይናገራሉ።
ይህ ቀድሞ መሠረቷ አሁን ደግሞ ምልክቷ የኾነው ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ለባሕር ዳር ከተማ ልዩ የቱሪዝም መዳረሻ ኾኗል።
ቤተ ክርስቲያኑ ከተመሠረተ ጀምሮ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሰባር አፅሙ ክብረ በዓል በየዓመቱ ጥር 18 ቀን በደመቀ ሁኔታ ይከበራል።
ይህ በዓል ከመንፈሳዊ ክብሩ በተጨማሪ በከተማዋ የቱሪዝም እድገት ውስጥ ጉልህ ሚና ያለው ክስተት ነው።
ቤተ ክርስቲያኑ በጣና ሐይቅ ዳርቻ መገኘቱ ውብ ተፈጥሯዊ እይታን ከመንፈሳዊ እና ከሥነ ባሕል ጋር በማጣመር ለጎብኚዎች ልዩ ስሜት ይፈጥራል።
በተለይ በበዓሉ ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን እና ጎብኚዎች ወደ ሥፍራው በመምጣት ለሃይማኖታዊ ቱሪዝም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ።
በበዓሉ ቀን ታቦቱ ከመንበሩ ወጥቶ በካህናት ተከብቦ፣ ምዕመናን በባሕላዊ አልባሳት አጊጠው በዝማሬ እና በክብር ሥነ ሥርዓት ይሰበሰባሉ። ከጣና ሐይቅ የሚነፍሰው ነፋስ ከዝማሬ ድምፅ ጋር ተቀላቅሎ በዓሉን የተለየ ውበት ያላብሰዋል።
በዕለቱም ታቦቱ በካህናት እና በዘማሪያን ታጅቦ በጣና ሐይቅ ላይ ይከበራል፤ የታንኳ ቀዘፋ ትርኢትም የበዓሉ ትልቅ ድምቀት ነው።
የቅዱስ ጊዮርጊስ ሰባር አፅሙ መንፈሳዊነትን፣ ታሪክን እና ቱሪዝምን በአንድ ላይ ያቀናጀ የባሕር ዳር ዋና መለያ ነው። በተገቢ ድጋፍ እና ልማት ወደ ሀገር አቀፍ የቱሪዝም መዳረሻነት ለማሳደግ “ከጥርን በባሕር ዳር” ሁነቶች አንዱ አካል ተደርጎ እየተሠራም ነው።
ዘጋቢ:- ሰናይት በየነ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!









