የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን ጥቅም ማኅበረሰቡ አውቆ እንዲጠብቀው እየተሠራ ነው።

0
27
ደባርቅ: ጥር 21/2018 ዓ.ም (አሚኮ) የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በአምስት ወረዳዎች እና በአንድ ከተማ አሥተዳደር በጥቅሉ በ42 ቀበሌዎች ይዋሰናል::
ፓርኩ በ1958 ዓ.ም በ136 ኪሎ ሜትር ስኩዌር የቦታ ስፋት በመከለል በሀገሪቱ ከተቋቋሙት ፓርኮች መካከል አንዱ ነው።
የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክን በዘላቂነት ለመንከባከብ እና የቱሪስት መዳረሻነቱን ለማስፋት በሚደረገው ጥረት የማኅበረሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ ሊኾን እንደሚገባ የሰሜን ጎንደር ዞን ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ገልጿል።
የመምሪያው ኀላፊ መዝናናት ጣዕመ የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መኾኑን ገልጸዋል።
ወደ ፓርኩ የሚመጡ ጎብኝዎች ቁጥር በተለያዩ ምክንያቶች ተቀዛቅዞ መቆየቱን ጠቁመው በአሁኑ ጊዜ የተወሰኑ መሻሻሎች መታየቱንም አብራርተዋል።
ወደፊት የፓርኩን የቱሪዝም መዳረሻነት ለማስፋት፣ ለማስተዋወቅ እና በጥናት ለመደገፍ እንደሚሠራም ገልጸዋል።
የመምሪያው የቅርስ ጥበቃ እና እንክብካቤ ቡድን መሪ ካሳሁን ንግሩ የፓርኩን ደኅንነት ለማረጋገጥ እና የቱሪዝም መዳረሻነቱን ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከማኅበረሰቡ ጋር ተከታታይ የውይይት መድረክ ሲካሄድ መቆየቱን አብራርተዋል።
በዚህም ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከሌሎችም የማኅበረሰብ አካላት የተውጣጣ ግብረ ኀይል በማቋቋም ወደ ሥራ መገባቱን አብራርተዋል።
አሚኮ ያነጋገራቸው የጃናሞራ ወረዳ ኗሪዎች የፓርኩን ደኅንነት በመጠበቅ እና በመንከባከብ በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በሌሎች ዘርፎች ተጠቃሚ መኾን እንደሚገባም አንስተዋል።
እንደማኅበረሰብ ለፓርኩ ሊደረግለት የሚገባውን ጥበቃ እና እንክብካቤ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሠሩም አብራርተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here