አቆልቋይ በአገው ማኅበረሰብ ዘንድ!

0
13
ባሕር ዳር: ጥር 24/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አቆልቋይ በበርካታ አካባቢዎች የተለመደ የማኅበራዊ እሴት ነው። መረዳዳትን፣ መተባበርን፣ አብሮነትን እና ኅብረትን መሠረት ያደረገ ጠንካራ የማኅበረሰብ መሥተጋብር የሚታይበት የባሕል መገለጫም ነው።

ይህ ሲኾን ታድያ በማኅበረሰብ መካከል የጠነከረ ትስስር እንድኖር ያደርጋል። በደስታም ኾነ በሐዘን ጊዜ በርካታ የሰው ቁጥር በሚታደምበት፤ ድግስ እና ዝግጅትም በቡድን በመኾን የሚስተናገድበት የመተጋገዝ ማሳያ ነው። በተለይ ደግሞ በገጠሩ ማኅበረሰብ ዘንድ አቆልቋይ የተለመደ ነው። የአቆልቋይ ሥነ ሥርዓት እንደሌሎቹ አካባቢዎች ሁሉ በአገው ማኅበረሰብ ዘንድም አንዱ ባሕላዊ እሴት ኾኖ የዘለቀ ነው። በአገው የፈረሰኞች ማኅበርም ከሚከናወኑት ሥርዓቶች መካከል አቆልቋይ የመስተንግዶ ሥርዓት አንዱ ኾኖ ይከወናል።
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ ተተኪ ኀላፊ ወለሊ ጌቴ አቆልቋይ የፈረሰኞች በዓል ሲያከበር በስፍት እንደሚተገበር ገልጸዋል። በአቆልቋይ ምግብ እና መጠጥ የሚቀርብበት ባሕላዊ ቁሳቁሶችን በመጠቀም መኾኑንም አንስተዋል። ለአብነትም ጠላውን በገምቦ፣ እንጀራውንም በመሶብ እና በሌሎችም የእደ ጥበብ ውጤቶች ይቀርብበታል ነው ያሉት። ይህም ባሕላዊ እሴቱን ጠብቆ መዝለቁን የሚያሳይ ስለመኾኑም አመላክተዋል።
የአገው ፈረሰኞች ማኅበር ገንዘብ ያዥ የኾኑት አለቃ አስፋው አጋዥ አቆልቋይ በወረዳ እና በቀጣና በመመደብ በየተራ መስተንግዶ የሚከናወንበት ሥርዓት መኹኑን ተናግረዋል። በዚህ ሥርዓት ፈረሰኛው ፈረስ ሲጋልብ ውሎ ምግብ ተጠቅሞ እንዲሄድ የሚደረግበት ነው ብለዋል። ባሕሉ ጥንትም የነበረ ከአያቶቻችን የተቀበልነው ሥርዓት ነው የሚሉት አለቃ አስፋው ሁሉም ፈረሰኞች የሚስተናገዱበት ስለመኾኑም ነው ያነሱት። የአገው ፈረሰኞች ማኅበር አባል የኾኑት አዳሙ ብርሃን በማኅበራቸው አቆልቋይ ይዘው ፈረሰኛውን ሲያስተናግዱ አግኝተናቸዋል። አቆልቋይ ጠቀሜታው ሰፊ ቁጥር ያለውን የፈረሰኛ ማኅበር የሚስተናገድበት ሥርዓት መኾኑን ተናግረዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here