የእምቅ ፀጋዎች ባለቤት የኾነው የዓባይ ሸለቆ

0
269

ባሕር ዳር: የካቲት 08/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ዙሪያ ገባውን በጥልቀት ለቃኘ በአማራ ክልል የሃብት ምንጭ የኾኑ ጸጋዎቹ ብዙ ናቸው፡፡ ክልሉ የበርካታ ቱሪስቶች መዳረሻ ቢኾንም በጸጋው ልክ አልለማም።

በአማራ ክልል ሁሉም ዞኖች ለሀገር ውስጥም ኾነ ለውጭ ዜጎች አግራሞትን የሚያጭሩ በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች አሉ፡፡ በዛሬው ቅኝታችን ወደ ምዕራብ አማራ ጎጃም ምድር እናቀናለን፡፡ ይህ ቀየ ብዙዎቹ የሚናፍቁት፣ ያዩትም መልሰው እስኪያዩት የሚጓጉለት አካባቢ ነው፡፡

የጎጃም ሰዎች ቅን እና እንግዳ ተቀባይ ስለመኾናቸው ያየ ሁሉ ይመሰክርላቸዋል፡፡ ውሎ ላደረ፣ ለተዛመደ ደግሞ በቀየው ያለውን ውብ ተፈጥሮ እና የቱሪስት መስህብ ይበልጥ እንዲገነዘብ ይረዳዋል፡፡ ከጎጃም ውብ ሥፍራዎች ውስጥ የዓባይ ሸለቆ እና የአካባቢው ልዩ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ አንዱ ነው፡፡

ይህ አካባቢ ካለው ተፈጥሯዊ አቀማመጥ እና ከትርፍርፍ ጸጋው አኳያ በብዙዎች ተመራጭ ሥፍራ ለመኾን ችሏል፡፡ “ይታደሏል እንጅ አይታገሉም” እንዲሉ ይህ ሥፍራ በተመራማሪዎች ዓይን ገብቶ ብዙ ጊዜ የሚያጠኑት ስፍራም ነው፡፡

ዶክተር ይርመድ ደመቀ ፣ አቤል በላይ፣ ዘውዱ ገዛሃኝ እና ቢኒያም ይርመድ የተባሉ ተመራማሪዎች ይህን ሥፍራ ለረዥም ጊዜ በማስተዋል በጥልቀት አጥንተውታል፡፡ እንደ አጥኝዎቹ ገለጻ ከኾነ የዓባይ ሸለቆ እና አካባቢው ብዙ ፀጋዎች ያሉት ድንቅ ሥፍራ ነው ይላሉ፡፡ በርካታ የውጭ ዜጎችን የሚስቡ ገጸበረከቶችም እንዳሉት ነው በጥናታቸው ያረጋገጡት፡፡
ዶክተር ይርመድ ደመቀ በ2015 ዓ.ም ያካሄዱትን ጥናታቸውን መሰረት አድርገው እንደሚናገሩት የዓባይ ሸለቆ እና አካባቢው ውስጥ 155 የአዕዋፍ ዝርያዎች ይኖራሉ፡፡ እነዚህም አዕዋፋት ጎብኝዎችን የሚስቡ ስለመኾናቸው ነው የሚናገሩት፡፡

ዶክተር ይርመድ በጥናታቸው ካገኟቸው የአዕዋፍ ዝርያዎች ውስጥ 14 ያህሉ በሌላ በየትኛውም የዓለም ጥግ የማይገኙ መኾናቸው አካባቢውን ልዩ ያደርገዋል፡፡ ይህን አካባቢ ማስተዋወቅ ለሀገርም ኾነ ለአካባቢው ያለው ጠቀሜታ በቀላሉ የሚታይ አለመኾኑንም ያስረዳሉ፡፡

ካገኟቸው ብርቅየ የአዕዋፍ ዝርያዎች መካከል ሶረኔ ቆቅ፣ የደጋ ጋጋኖ፣ የአቢሲኒያ እርግብ፣ ባለጥቁር ክንፍ በቀቀን፣ ሽልምልም ጋርደም፣ የአቢሲኒያ ግንደ ቆርቁር፣ የሩፔል የቋጥኝ ወፍ፣ ባለ ነጭ ክንፍ የቋጥኝ ወፍ፣ የአቢሲኒያ ጨረባ፣ ራሰ ቦቃ ቁራ፣ የኢትዮጵያ ጫጫቴ፣ ነጭ ማንቁር ወማይ፣ ጥቁር ራስ ዘረ በል፣ እና ጀርባ ቢጫ ዘረ በል መኾናቸውን በጥናታቸው አሳይተዋል፡፡

የዓባይ ሸለቆ እነዚህን አይነት የእንስሳት ሃብቶችን እና በርካታ ሀገር በቀል ዕጽዋትን እንዲሁም በርካታ ያልተዳሰሱ እና ተጨማሪ ጥናትን የሚፈልጉ ፀጋዎችን አምቆ የያዘ ነው። ይህንን ፀጋ በጥናት ለይቶ ማወቅ፣ ማስተዋወቅ እና ወደ ሃብት ቀይሮ ጥቅም ላይ ማዋል ከትውልዱ የሚጠበቅ ነው።

ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here