የባሕል አምባሳደሩ የጉና የሙዚቃ እና ቴአትር ቡድን

0
64

 

ባሕር ዳር: የካቲት 18/2018 ዓ.ም (አሚኮ) ጥበብ የሰው ልጅ ባሕሉን፣ ማንነቱን እና ታሪኩን ሰንዶ የሚይዝበት ሕያው መዛግብት፣ ራሱን የሚመለከትበት መስታወት ነው። ሁለንተናዊ ስሜቱን ከሚገልጽባቸው የጥበብ ዘርፎች ውስጥ ደግሞ ሙዚቃ እና ቴአትር ከቀዳሚዎቹ ውስጥ ይጠቀሳሉ። ​ተስፋ እና ፍላጎትን በማንጸባረቅም እንደ ድምጽ ኾነው ያገለግላሉ። ከማኅበራዊ ፋይዳቸው ባለፈ የሀገርን ገጽታ በመገንባት ረገድ ከፍተኛ ጥቅም አላቸው።

የአማራ ክልል ደግሞ ታዋቂ የሙዚቃ እና የቴአትር ባለሙያዎችን በማፍራት ተጠቃሽ ነው። ፋሲለደስ፣ ግሽ ዓባይ፣ የላሊበላ የኪነት ቡድኖች በኢትዮጵያ የባሕል ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ትልቅ አሻራ ካሳረፉት ውስጥ ከቀዳሚዎቹ ማንሳት ይቻላል። አሁን ላይ ከክልሉ አልፎ ሀገርን እያስጠሩ ከሚገኙ ውስጥ ደግሞ የጉና የሙዚቃ እና ቴአትር ቡድን ይገኝበታል።

በታሪካዊቷ ደብረ ታቦር ከተማ መቀመጫውን ያደረገው የጉና የሙዚቃ እና ቴአትር ቡድን ከተመሠረተ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ የጎንደርን ብሎም የክልሉን ሕዝብ ባሕል፣ ወግ፣ ታሪክ፣ የአኗኗር ዘይቤ እና አለባበስ ተጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፉ እየሠራ ይገኛል። በርካታ ባለሙያዎችንም እያፈራ ይገኛል።

የባሕል ቡድኑ ድምቀት ከኾኑት መካከል ደግሞ ድምፃዊት የስይት ዓለምነው አንዷ ናት። ከትምህርት ቤት ክበባት ተነስታ የባሕል ቡድኑን በመቀላቀል የአካባቢውን ባሕል እንዲያድግ የድርሻዋን እየተወጣች ትገኛለች። ለአስር ዓመታት ያህልም በቡድኑ እያገለገለች ትገኛለች። በተለይም ደግሞ የፍቅርአዲስ ነቃጥበብን፣ የሐመልማል አባተን፣ የአምሳል ምትኬን እና ሌሎች የሙዚቃ ሥራዎችን በይበልጥ ትጫዎታለች።

ወደፊት ክልላዊ እና ሀገራዊ ሙዚቃዎችን በመሥራት ለሕዝብ ለማበርከት እና እንደ ሀገር የባሕል አምባሳደር ለመኾን ተዘጋጅታለች።

ዘመኑን የሚመጥኑ ግብዓቶችን ማሟላት ከተቻለ የተሻለ ሥራዎችን እንደሚሠሩ ነግራናለች።

ሌላው በድምፃዊነት እየሠራ የሚገኘው ወጣት ያብባል ምስጋናው ሙዚቃ ማኅበረሰብን ለማስተማር እና መልዕክት ለማስተላለፍ የጠነከረ አቅም ያለው መሳሪያ እንደኾነ ይናገራል። የፋሲል ደሞዝ፣ የደረጀ ደገፋው፣ የሀብተሚካኤል ደምሴን፣ የቴዎድሮስ ታደሰን፣ የጋሽ ጥላሁን ገሰሰን፣ የአበበ ተካን እና የቴዎድሮስ ካሳሁን ሙዚቃዎችን እያዜመ ያደገ ስለመኾኑ ገልጿል።

በብሔራዊ ቴአትር በወጣው ቅጥር ተፈትኖ ማለፉን እና ጥሪ እየተጠባበቀ እንደሚገኝም ነግሮናል። የሙዚቃ ቡድኑ ለሙዚቃው ኢንዱስትሪ እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ ቀላል እንዳልኾነ ገልጿል።

ባሕል ቡድኑ የተሻለ ደረጃ እንዲደርስ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው አመላክቷል። በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚዘጋጁ የ “ታለንት ሾው” ውድድሮች ላይ ለመሳተፍ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ነው።

የጉና የባሕል፣ ሙዚቃ እና ቴአትር ቡድን
አስተባባሪ ቴዎድሮስ ካሳሁን እንዳለው ቡድኑ በአማራ ክልል በኪነ ጥበብ ዘርፉ በተለይም በባሕላዊ ውዝዋዜ እና ሙዚቃ ላይ ስማቸው ከሚጠሩ የባሕል ቡድኖች ውስጥ አንዱ ነው። በርካታ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ለሀገር ማበርከቱንም ገልጸዋል። አስተባባሪው እንደተናገረው የባሕል ቡድኑ ከኪነ ጥበብ ሥራዎቹ ባሻገር በልማት እና በማኅበራዊ ሥራዎችም ማኅበረሰቡን እያገለገለ ነው።

የባሕል ቡድኑ በአጫጭር ድራማዎች እና ሌሎች የጥበብ ሥራዎች የክልሉ ማኅበረሰብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር እየሠራ መኾኑንም ገልጸዋል። በማሊዥያ በተዘጋጀ የሙዚቃ እና ቴአትር መድረክ ላይ በመሳተፍ የሀገሪቱን ባሕል እና ወግ ማስተዋወቁን በማሳያነት አንስተዋል።

በቀጣይም የባሕል ቡድኑን ወደ ባሕል ማዕከል ለማሳደግ ጥናት እየተደረገ መኾኑን ጠቅሷል። የባሕል ቡድኑን አቃፊነት በማሳደግ፣ ራሱን ችሎ ቋሚ ገቢ እንዲያመነጭ እና ተሰጥኦ ያላቸው ወጣቶች ወደ ሙያው እንዲገቡ እየተሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት።

ቡድኑ የራሳቸውን ሙዚቃ ያሳተሙ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ የአይዶል ውድድሮች አሸናፊ የኾኑ እና አሁንም የራሳቸው ሥራ እየሠሩ የሚገኙ ወጣቶችን ማፍራቱንም ገልጸዋል። የባሕል ቡድኑ የተሻለ ሥራ ሠርቶ እንዲታይ ደግሞ ሁሉንም ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳደር ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት መምሪያ የባሕል እሴቶች ኢንዱስትሪ ልማት ቡድን መሪ ታደሰ ቢያድጌ የባሕል ቡድኑ ከተመሠረተ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ የክልሉን ባሕል፣ እሴት፣ ታሪክ፣ አኗኗር ዘይቤ፣ አለባበስ እና የማኅበረሰቡ ወግ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፉ እያስተዋወቀ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የባሕል ቡድኑን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ በደብረታቦር ከተማ ደረጃውን የጠበቀ የባሕል ማዕከል እየተገነባ መኾኑን ተናግረዋል።

የባሕል ቡድኑን ይበልጥ ለማጠናከር ከደቡብ ጎንደር ዞን አሥተዳደር፣ ከደብረ ታቦር ከተማ እና ከደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ጋር እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል።

ብቁ የኪነ ጥበብ ሰዎችን ለማፍራት ባሕል ቡድኑን መደገፍ የሁሉ ኀላፊነት ሊኾን እንደሚገባም ጠይቀዋል። የባሕል ቡድኑ አሁን ላይ 22 አባላት ያሉት ሲኾን ከእነዚህ ውስጥ 10 ተወዛዋዦች፣ አምስት ድምፃውያን፣ አምስት የሙዚቃ ተጫዎች እና ሁለት ድርሰት አዘጋጆች ናቸው።

ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here