የአድዋ ድል ባለውለታዋ-ወረኢሉ!

0
58
ባሕርዳር፡ የካቲት 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን ከሚገኙ ወረዳዎች ውስጥ አንዷ፣ በበርካታ የተፈጥሮ ሃብቶች የታደለች እና ደምቆ የሚነገር ታሪክ ባለቤትም ናት ወረኢሉ።
በታሪክ ከአድዋ ጦርነት የክተት ዘመቻ አዋጅ ጋር ተያይዞ ስሟ ይነሳል። አጼ ምኒልክ “ዘመቻየ በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረኢሉ ከተህ ላግኝህ” በማለት የኢትዮጵያ ሠራዊት በአንድ ማዕከል እንዲሰባሰብባት የመረጧት ቦታም ናት፡፡
የወረኢሉ አካባቢ ነዋሪ እና የወረኢሉ ማኅደረ ኢትዮጵያ የታሪክ መጽሐፍ ደራሲ ክበር ጌታቸው በኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን በአፍሪካ ታሪክ የመጀመሪያ እና ብቸኛ የሚባለው ግዙፉ የጦር ሠራዊት ወረኢሉ ላይ መክተሙን ነው የተናገሩት።
በአድዋ ጦርነት ከአንድ መቶ ሺህ በላይ የሚገመት የኢትዮጵያ ሠራዊት ወረኢሉ ላይ እንደተሰባሰበም ታሪክን ከመጽሐፋቸው ጋር አጣቅሰው ነግረውናል። የካቲት 23/1888 ዓ.ም አድዋ ላይ ለተመዘገበው ድል ግንባር ቀደም አስተዋጽኦ እንዳበረከተችም ጠቅሰዋል፡፡ የአድዋ ጦርነት ዘመቻ ምክር የጸደቀባት እና ውሉ የጸናባት ቦታ መኾኗንም አንስተዋል።
ወረኢሉ በአድዋ ዘመቻ ቀላል የሚባሉ የጦር መሳሪያዎች (ጦር፣ ጎራዴ፣ ጋሻ…) ተዘጋጅተውባታል፤ የጦር መሳሪያ ማከማቻ ኾናም አገልግላለች ነው ያሉት። ለዘመቻ የሚኾን እርጥብ እና ደረቅ ስንቅ ማዘጋጃ ኾናም አገልግላለች ብለዋል። ወረኢሉ ባላት ታሪክ ልክ ግን ታሪኳን የማስተዋወቅ ሥራዎች ውስንነት እንዳለ ጠቅሰዋል።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር እና ተመራማሪ ገረመው እስከዚያ(ዶ.ር) ወረኢሉ አጼ ምኒልክ ከመንገሣቸው በፊትም ጊዜያዊ ማዕከል አድርገው እንደተጠቀሙባት ተናግረዋል። ከነገሡ በኋላ ደግሞ ለንጉሡ ማዕከል ኾነው ካገለገሉ ሦሥት ቦታዎች (አንኮበር፣ እንጦጦ እና ወረኢሉ) መካከል አንዷ መኾኗን ነው የጠቀሱት።
በአድዋ ጦርነት ደግሞ ወረኢሉ ወደ አድዋ ለመተላለፍ ስትራሄጅካዊ ቦታ በመኾኗ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጣ የኢትዮጵያ ሠራዊት የሚገናኝባት እንደኾነች ቀን ቆጥረው አዋጅ በማስነገር በጥቅምት እኩሌታ 1888 ዓ.ም እንደተገናኙባትም ገልጸውልናል።
የጦር ዘመቻ ሲደረግ የግድ ቅድመ ዝግጅት ይደረጋል ያሉት የታሪክ መምህር እና ተመራማሪው በአሁኑ የጦር ስልት ማዘዣ ጣቢያ እንደሚባለው ኾና አገልግላለች ነው ያሉት። የአድዋ ድል የመላ ኢትዮጵያውያን ትብብር እና አሻራ ያረፈበት፤ የጥቁር ሕዝቦች ድል መኾኑንም ተናግረዋል። አሁን ላይ ኢትዮጵያውያን ከእንደዚህ ዓይነት ታሪኮች ትብብርን መማር ይገባቸዋል ብለዋል።
የአማራ ክልል ባሕል ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ የቱሪዝም ልማት ዳይሬክተር መልካሙ አዳም ከአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ በአማራ ክልል በርካታ ታሪኮች የተከናወኑባቸው፣ የቀደምት አባቶች ጥበብ ያረፈባቸው የቱሪስት መዳረሻዎች መኖራቸውን ተናግረዋል። ለጎብኝዎች መዳረሻ እንዲኾኑ ደግሞ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ እንደኾነ ነው የገለጹት።
ባለሀብቶች ታሪካዊ ቦታዎች እና ቅርሶች የሚገኙባቸውን አካባቢዎች በማልማት በአገልግሎት ዘርፍ ተሠማርተው ለጎብኝዎች አገልግሎት እንዲሰጡም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here