ባሕር ዳር: የካቲት 22/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አንዳንድ ጉዳዮች መነሻነታቸው ለጥሩ ይኾንና ለዘመናት ሲታወሱበት፣ ሲዘከሩበት ይኖራሉ።
ውጫሌ ምን እንኳን ጦርነት ጥሩ ነገር ባይኾንም ለዓድዋ ድል ምክንያት የኾነው ውል የተፈረመበት ቦታ በመኾኑ የዓድዋ ድል ሲነሳ ሁሌም ስሙ አብሮ ይነሳል።
ውጫሌ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ከወልድያ ወደ ደሴ በሚወስደው መንገድ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በአምባሰል ወረዳ ውስጥ የሚገኝ ቦታ ነው። አካባቢው ደጋማ እና በተራራዎች የተከበበ ነው።
ውጫሌ በታሪክ ጎልታ የምትታወቀው በአጼ ምኒልክ እና በጣሊያኖች መካከል የተፈረመው የውጫሌ ውል የተከናወነበት ቦታ በመኾኗ ነው። ይህ ውል በሁለቱ ሀገራት መካከል የወዳጅነት ስምምነት ተብሎ ቢጀመርም፣ በውስጡ ግን ሴራ ነበረበት።
የውጫሌ ውል የዓድዋ ድል ታላቅ የታሪክ ምዕራፍ እንዲኾን ያደረገ ምክንያት ነው።
ሚያዝያ 25 ቀን 1881 ዓ.ም በንጉሥ ምኒልክ እና በኢጣሊያው ተወካይ ካውንት አንቶኔሊ መካከል በውጫሌ የተፈረመው ይህ ውል ከነበሩት 20 አንቀጾች መካከል ጥልን የፈጠረው አንቀጽ 17 ነው።
በዚህ አንቀጽ በአማርኛ እና በጣሊያንኛው ላይ የተቀመጠው ትርጉም መለያየት ነው ለጦርነቱ መነሻ የኾነው። በሁለቱ ሀገራት የነበረውን ግንኙነት ከመልካም ወዳጅነት ወደ መራራ ጦርነት ቀይሮታል።
ደራሲ ጳውሎስ ኞኞ “አጤ ምኒልክ” በሚለው መጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት የአማርኛ ጽሑፉ ”የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ከአውሮፓ ነገሥታት ለሚፈልጉት ሁሉ በኢጣሊያ መንግሥት አጋዥነት መላላክ ይቻላቸዋል” ይላል። ይህም ፈቃደኝነትን ወይም አማራጭን የሚያመላክት ነው።
የጣሊያንኛው ደግሞ “የኢትዮጵያ መንግሥት ከውጭ ሀገር መንግሥታት ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት በኢጣሊያ መንግሥት አማካይነት ማድረግ ይገባዋል“ ይላል፡፡ ይህ ደግም ግዴታን የሚጥል በመኾኑ ጣሊያን ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት ያሰበችበት ነው። በንጉሥ ምኒልክ በኩል ግን የሀገርን ሉዓላዊነት የሚጋፋ ኾኖ ተገኝቷል። ንጉሥ ምኒልክ ውሉ እንዲታረም ቢጠይቁም ጣሊያኖች ፈቃደኛ አልኾኑም።
ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ በመባል የሚታወቁት እቴጌ ጣይቱ ታዲያ “እኔ ሴት ነኝ ጦርነት አልወድም፤ ነገር ግን ይሄን የመሰለ የሀገር ክብር የሚነካ ውል ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ” በማለት ለንጉሡ “ይስሙ ንጉሥ” በሚል ያደረጉትን ታሪካዊ ንግግር መሰረት በማድረግ በውጫሌ ውሉ የተፈረመበት ቦታ “ይሥማ ንጉሥ” ተብሎ እንደተጠራም ይነገራል፡፡
እቴጌ የወሰዱት ጠንካራ አቋም ለጦርነቱ መነሳሳት ጉልህ ሚናም ነበረው። በመጨረሻም በ1885 ዓ.ም አጼ ምኒልክ የውጫሌን ውል በይፋ መሰረዛቸውን ለአውሮፓ መንግሥታት አሳውቀዋል።
በወቅቱ የኢጣሊያ መንግሥት የውሉን መፍረስ እንደ ጦርነት አዋጅ በመቁጠር ኢትዮጵያን በመውረር እንደሌሎች አውሮፓ ሀገራት ለቅኝ ግዛት አሰበቻት። ይህ ግፊት ነው መላው ኢትዮጵያዊ በሀገር ፍቅር ስሜት ተነሳስቶ ወደ ዓድዋ እንዲተም እና ታሪካዊውን የኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን የመላው አፍሪካ፣ የጥቁር ሕዝቦች ድል የኾነውን የዓድዋ ድል እንዲቀዳጅ ያደረገው።
ታዲያ ታሪካዊው ቦታ ውጫሌ ስሙን ከማንሳት ባለፈ አሁን ምን ላይ ይገኛል?
በአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አበበ እምቢያለ የይሥማ ንጉሥ ታሪካዊ ቦታ በክልሉ መንግሥት በጀት ቢሮው ልዩ ሙዚየም እንዳስገነባበት ነግረውናል።
ልዩ ሙዚየሙ የዓድዋ ድልን ታሪካዊ መነሻዎች እና ውጤቶች ለትውልዱ ሊያሳይ የሚችሉ ቅርሶች ስብስብ እንዲኖረው የታሰበ ነው ብለዋል። ከሙዚየሙ በተጨማሪ የአጼ ምኒልክ እና የእቴጌ ጣይቱ ሐውልት መሠራቱንም አንስተዋል።
ሙዚየሙ ተገንብቶ ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት እንደደረሰበትም አስታውሰዋል። አሁን ላይ በ10 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ጥገና ለማካሄድ በጨረታ ሂደት ላይ መኾኑን ተናግረዋል።
ሙዚየሙን ለማደራጀትም ቁሳቁስ የማሟላት እና ቅርስ የማሰባሰብ ሥራዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሠራ ነው ብለዋል።
ውጫሌ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይኾን ለጥቁር አፍሪካውያን የድል ጥንስስ የጀመረበት ቦታ በመኾኑ ለጎብኝዎቹ ምቹ የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።
የሀገርን ታሪክ የሚዘክረው ሙዚየም ወደ ሥራ ሲገባ ከሎጎ ሐይቅ ሪዞርት በቅርብ ርቀት የሚገኝ በመኾኑ አዳጊ የቱሪስት መዳረሻ እንዲኾን የሚያስችል እንደኾነ ነው የገለጹት።
ዘጋቢ፡ ፍሬሕይወት አዘዘው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን









