በታላቁ የዜማ አባት የተሰየመው ያሬድ የባሕል ቡድን

0
32
ፍኖተሰላም: መጋቢት 15/2018 ዓ.ም (አሚኮ) አካባቢውን ባሕል በማስተዋወቅ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው። አንጋፋው እና ስመ ጥሩ ዋሸራ የባሕል ቡድን በተለያዩ ምክንያቶች ሲፈርስ ከዚሁ የባሕል ቡድን ውስጥ በነበሩ በተወሰኑ አባላት በ2008 ዓ.ም ነው የተቋቋመው “ያሬድ የባሕል ቡድን”።
በምዕራብ ጎጃም ዞን በጃቢጠህናን ወረዳ ውስጥ የሚገኘው በታላቁ የዜማ አባት ቅዱስ ያሬድ የተሰየመው ”ያሬድ የባሕል ቡድን” የኪነ ጥበብ እና የባሕል ሥራዎችን በተለያዩ መድረኮች በማቅረብ እና በማንፀባረቅ አበርክቶ እያደረገ ነው።
በባሕል ቡድኑ ውስጥ የባሕል ሙዚቃ የድምጽ ተጫዋች የኾኑት ድምፃዊ በልስቲ ከበደ እና ድምፃዊት መቅደስ ሙሔ በቡድኑ ውስጥ የአካባቢውን እምቅ ባሕል የማስተዋወቅ ሥራዎችን እያከናወኑ መኾናቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይ ከባሕል ቡድኑ ተሳትፎ ባሻገር የራሳቸውን የሙዚቃ ሥራዎች ለመሥራት አልመው እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ሌላው የሙዚቃ ተወዛዋዥ ወጣት ልደቱ ዘላለም በዞኑ ዳሞት ምት እና ዝናብ እንቅጥቅጥ የሚባሉ የውዝዋዜ አይነቶችን በማስተዋወቅ እና ለትውልድ በማሻገር ላይ መኾናቸውን ተናግሯል። ከዞኑ ባሻገር ያሉ የውዝዋዜ አይነቶች ላይም ሰፊ ሥራ እየሠሩ እንደሚገኙ ነው ያስረዳው።
በባሕል ቡድኑ ውስጥ ሁለገብ የሙዚቃ ተጫዋቾች እና የቡድኑ አስተባባሪ ዘመን እሱባለው የባሕል ቡድኑ በ12 አባላት በ2008 ዓ.ም መመስረቱን ተናግሯል። አሁን ላይ 21 አባላት ላይ ደርሷል።
የወረዳውን ባሕል በማስተዋወቅ እና ተተኪ የባሕል ቡድን አባላትንም ለማፍራት እየተጋ እንደሚገኝም ገልጿል። በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ባሕል፣ ወግ፣ አለባበስ እና አጊያጊያጥ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅም የባሕል ቡድኑ እየሠራ እንደሚገኝም ተናግሯል።
የባሕል ቡድኑ የሚያከናውናቸውን ሥራዎች የማስተዋወቅ ውጥንን ውጤታማ ለማድረግ ከወረዳው ባለፈ ሁሉም እገዛ ማድረግ እንደሚገባው ገልጿል።
የባሕል ቡድኑ ክልሉን በመወከል በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚከናወነው የባሕል እና ኪነ ጥበብ ፌስቲቫል ላይ ተሳትፎ ውጤታማ ለመኾን ሰፊ ዝግጅት እያደረጉ መኾናቸውንም አስረድቷል።
የጃቢ ጠህናን ወረዳ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዓለም ገረመው ያሬድ የባሕል ቡድን የአካባቢውን ባሕል በማስተዋወቅ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች እንዲሳለጡ ከፍተኛ ሚና እየተወጣ መኾኑንም ተናግረዋል።
የባሕል ቡድኑን በማጠናከር ተተኪ ከያኒያንን ለማፍራት የወረዳው ምክር ቤት አስፈላጊ ድጋፎችን እያደረገ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
ቡድኑ ከወረዳው ባለፈ እስከ ዞን እና ክልል አቀፍ ደረጃ የኪነ ጥበብ እና የባሕል ሥራዎችን በማቅረብ ሰፊ ሥራ ማከናወኑንም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here