ድንቅ ተፈጥሮ አባ ማታራት ፏፏቴ።

0
36

 

ባሕር ዳር፡ መጋቢት 16/2018 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በሰሜን ጎጃም ዞን በደቡብ አቸፈር ወረዳ፣ ከዱርቤቴ ከተማ ወደ ዳንግላ የሚወስደውን አስፋልት ተከትሎ ጥቂት እንደተጓዙ ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ በምትገኘው አብችክሊ ቀበሌ (ልዩ ስሟ ስብት ጎጥ) አንድ ተፈጥሮ ሳትሰስት የለገሰችው ድንቅ ሀብት ይገኛል። ይህም “አባ ማታራት” ወይም “አሻር ፏፏቴ” ይሰኛል።

ከዱርቤቴ ከተማ አምስት ኪሎ ሜትር ብቻ ርቆ የሚገኘው ይህ ፏፏቴ፣ በግርማ ሞገስ ተቀምጦ ጎብኚዎችን በናፍቆት ይጠራል።

👉የስያሜው አመጣጥ በአፈ ታሪክ

የአካባቢው ነዋሪ አቶ ቻሌ አካሉ እንደገለጹት “አባ ማታራት” የሚለው ስያሜ ከአንድ አሳዛኝ እና አስገራሚ ታሪክ ጋር የተያያዘ ነው። በአንድ ወቅት አንዲት ሴት በክረምት ወራት መሽቶባት ውኃውን ለመሻገር ስትሞክር በጎርፍ ትወሰዳለች። ከፏፏቴው መውረድ ጋር ተያይዞ በሚፈጠረው ከፍተኛ የእንፋሎት ጭስ ምክንያት፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ “ሴትዮዋን ጭሱ አጠፋት (የማታ እራት አደረጋት)” በሚል እሳቤ “አባ ማታራት” የሚል ስያሜ እንደሰጡት ይነገራል።

👉የፏፏቴው ግርማ እና ተፈጥሯዊ ትርዒት

ፏፏቴው በሦሥት ቅርንጫፎች ተከፍሎ የሚፈስ ነው። ዋናው ፏፏቴ 35 ሜትር ገደማ ስፋት እና ወደ 21 ሜትር የሚጠጋ ቁመት አለው። ውኃው እንደ ክረምት ነጎድጓድ እየተስገመገመ ቁልቁል ሲወረወር የሚፈጥረው ትርዒት ለዐይን ይማርካል።

ውኃው ከአለቱ ጋር ሲጋጭ የሚፈጠረው ነጭ አረፋ፣ ፈታይ ሴት የነደፈችውን ንጹሕ ጥጥ መስሎ ይታያል።

ቁልቁል ወደ ገደላማው ስፍራ ሲወረወር ከአለቶቹ ንብርብር ጋር ተሳስሮ፣ ከሴት ልጅ ወገብ ላይ እንደሚታሰር ነጭ መቀነት ተጠቅልሎ ይታያል።

ፏፏቴው ከርቀት ሲታይ በነጭ ጉም የተከበበ እና የሚያካፋ ዝናብ የሚመስል የእንፋሎት ጭስ ይረጫል።

👉የአካባቢው ሥነ-ምሕዳር እና ድምቀት

አባ ማታራት በዙሪያው ባሉ ጥቅጥቅ ያሉ ደኖች ተከቦ የሚገኝ በመኾኑ የአካባቢው አየር ነፋሻማ እና በአበቦች መዓዛ የተሞላ ነው። እንደ ግራር፣ አባሎ፣ ሾላ፣ ችብሃ፣ ጨባ፣ ባሕርዛፍ፣ ዶቅማ እና አንዛምራ ያሉ ዕፅዋት ለፏፏቴው አረንጓዴ ካባ አልብሰውታል።

የዛፎቹ ውዝዋዜ፣ የአዕዋፋት ዝማሬ እና የፏፏቴው ሽብሻቦ ተዳምረው አካባቢውን የሐሴት ምንጭ አድርገውታል።

👉የቱሪስት መዳረሻነት አቅም

የደቡብ አቸፈር ወረዳ ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አቢዮት ታደለ እንደገለጹት በወረዳው ውስጥ አሻርን ጨምሮ 6 ፏፏቴዎች፣ 37 ቋሚ እና 1ሺህ 237 ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ይገኛሉ።

ምንም እንኳ ወቅታዊው የሰላም ሁኔታ ፈታኝ ቢኾንም ይህንን ድንቅ የተፈጥሮ ሀብት ለዓለም በማስተዋወቅ አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
👇👇👇
https://linktr.ee/AmharaMediaCorporation

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here