ባሕርዳር: መጋቢት 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን በመካከለኛው ክፍለ ዘመንም ኾነ በዘመናዊቷ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሚና የነበራቸው የነገሥታት፣ መኳንንት፣ ጀግኖች አርበኞች፣ የጥበብ ሰዎች እና ሌሎችም መፍለቂያ ነው፡፡
አጼ ዘርዓ ያዕቆብ፣ አፄ ሕዝብናኝ፣ መርዕድ አዝማች አመሐ የሱስ፣ መርዕድ አዝማች ወሰን ሰገድ፣ ንጉሥ ሳህለ ሥላሴ፣ አፄ ምኒልክ፣ ፊታውራሪ ገበየሁ፣ ተስፋ ገብረ ሥላሴ ዘብሔረ ቡልጋ፣ ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ እና ሌሎችም ከዚሁ ሥፍራ እንደተገኙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ትክል ድንጋዮች ያሉባቸው ሥፍራዎች፣ የቀብር ቦታዎች፣ ለተለያዩ አገልግሎቶች ተገንብተው የነበሩ የኪነ ሕንጻ ቅሬቶች፣ ቤተ መንግሥት፣ የሃይማኖት ተቋማት ታሪካዊ አምባዎች እና መካነ ቅርሶቻቸው፣ ገበያዎች (አልዩ አምባ)፣ የመገልገያ መሣሪያዎች ማምረቻ (ሸክላ፣ ብረታ ብረትና ባሩድ…) ሥፍራዎች፣ በዋናነት በአካባቢው የሚገኙ መስህቦች ናቸው።
ሰሜን ሸዋ ከያዘቻቸው ሕልቆ መሳፍርት ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ ቅርሶች መካከል ለዛሬ የሙሽራ ድንጋዮችን ልናስተዋውቃችሁ ወደናል።
ከአጣዬ ከተማ በስተምዕራብ አቅጣጫ 21 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን የገቱዘን ጋዲሎ ሜዳ ሰንጥቀው ሲጓዙ የተመልካችን እዝነ ሕሊና ሀሴት የሚያላብሱ የሰው ቅርፅ ያላቸውን ድንጋዮች ያገኛሉ፡፡
ጋዲሎ ሜዳ ደጃዝማች ምኒልክ ከመቅደላ እስር ቤት አምልጠው ሲሄዱ በምትካቸው በአፄ ቴዎድሮስ ተሹመው ከነበሩት አቶ በዛብህ ጋር ጦርነት ያደረጉበት ልዩ ሥፍራ ነው። ጦርነቱም በአፄ ምኒልክ አሸናፊነት ተጠናቅቋል።
በዚህ ቦታ የሚገኙት እነዚህ ድንጋዮች ‹‹የሙሽራ ድንጋዮች›› የሚል ስያሜ ተችሯቸዋል። ድንጋዮቹ የሰው ቅርጽ ያላቸው ትክል ድንጋዮች ናቸው። እነዚህ እጹብ ድንቅ ቅርጽን የተላበሱት “ሙሽራዎች” ከአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በፊት እንደተቀረጹ ይነገራል።
ድንጋዮቹ ስያሜያቸውን ያገኙበት መንገድ ትክክለኛ መረጃ ባይገኝም የተለያዩ መላምቶች ይቀርባሉ። ከነዚህ መላምቶች ውስጥ አንደኛው ጥንታዊ ሰዎች ለጌጥ እና ለምልክት ብለው የሠሯቸው ትክል ድንጋዮች ናቸው ይባላል። በሌላ አፈ ታሪክ ደግሞ ሰርገኞች ከአዲስ አምባ መጥቆሪያ ከሚባል ስፍራ ጋብቻ ፈጽመው ሲመለሱ የደረሰ ሰብልን እየረገጡ እና በሰብሉ ላይ”ሆ! እና ሎጋ”ን እየጨፈሩ ነበር በዚህ ጊዜ እህሉ ረገፈ። በዚህ ጊዜ የሰብሉ ባለቤትም አንገቱን ደፍቶ አዘነ። “ፈጣሪ ድንጋይ ያድርጋችሁ” ብሎ ሙሽሮችን ረገማቸው። ስያሜው ከዚህ እንደተወሰደ ይነገራል።
ከዚህ ባለፈ ግን የሙሽራ ድንጋዮች ታሪካዊ አመጣጥ ጥንታዊ ሰዎች ለአንድ ዓላማ ያቆሟቸው ትክል ድንጋዮች ናቸው ተብሎ ይታመናል። ምናልባትም ከአክሱም ዘመን በፊት ጀምሮ ሲያያዝ የመጣ የዕደ ጥበብ ውጤት እንደኾነም ይገመታል።
የሙሽራ ድንጋዮቹ ጾታ በግልጽ ይታወቃል። ሴቶች የጡት ቅርጽ አላቸው። ሴቷን ከወንድ የሙሽራ ድንጋይ በቀላሉ መለየት ይቻላል ማለት ነው። በአካባቢው ምሽት ላይ እንግዳ የኾነ ሰው አንገቱን አቀርቅሮ እየተጓዘ ነው እንበል፤ ድንገትም የሙሽራ ድንጋዮች አካባቢ ደርሶ ቀና ቢል ደንገጥ ብሎ “ጤና ይስጥልን! እንዴት አመሻችሁ!?” ማለቱ አይቀርም። የሙሽራ ድንጋዮች ቁርጥ የሰው ቅርጽ አላቸውና!
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!