ባሕር ዳር: መጋቢት 8/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር በርካታ የመስህብ ሥፍራዎች ይገኛሉ። ከእነዚህ እጹብ ድንቅ የመስህብ ሥፍራዎች መካከል አንዱ የዶንዶር ፏፏቴ ነው።
ፏፏቴው ከቻግኒ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ “መጠለያ” ተብሎ በሚጠራው ቦታ ይገኛል:: መነሻዎትን ቻግኒ ከተማ አድርገው በእግር፣ በብስክሌት፣ በሞተር ሳይክል ወይም በመኪና ተጉዘው ፏፏቴውን ያገኙታል።
ፏፏቴው “ዶንዶር” የተባለበት ምክንያት ደግሞ ከ”ዶንዶር” ወንዝ የሚነሳ በመኾኑ ነው። ከቻግኒ ከተማ ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ማኀበራዊ ገጽ ባገኘነው መረጃ ይህ ፏፏቴ በክረምት ወቅት በሰፊው እየተግተለተለ “ሿ” የሚል ድምጽ በማሰማት ይወርዳል። ጭስ እየፈጠረ ከ35 ሜትር በላይ ይወረወራል። በዚህ ጊዜም አካባቢውን እንደ ጸበል የሚረጨው የውኃ ፍንጣቂ አዕምሮን በሐሴት ያረሰርሳል።
ፏፏቴው ከላይ ተወርውሮ ከሥር ዓለቱ ላይ ሲያርፍ “ሿ!” ብሎ የሚፈጥረው ድምጽ አስገራሚ እና ጆሮ ገብ በመኾኑ አይጠገብም። የዶንዶር ፏፏቴ ከመስከረም እስከ ኅዳር ወራትም በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ጎብኝዎች በሰፊው ይጎበኛል።
የዶንዶር ወንዝ ዙሪያ ገባው ደግሞ በበጋ መስኖ ይለማበታል። በዚህ ፏፏቴ በቅርብ ርቀት ባለው ተራራ፣ ሸጥ፣ ጥብቅ ስፍራ እንደሚዳቋ፣ ድኩላ፣ ሰሳ፣ ዝንጀሮ፣ ጦጣ፣ ጅብ ከርከሮ፣ ነብር ያሉ የተለያዩ እንስሳት እንዲሁም አዕዋፍት በብዛት ይገኙበታል::
የቻግኒ እና አካባቢው ማኀበረሰብ ወዲህ በሥራ የደከመ አዕምሮውን ማዝናናት ሲሻ ወዲያ አንዳች የአዕምሮ መረበሽ ስሜት ሲያጋጥመው ከወጥረቱ ተንፈስ የሚለው ወደ ዶንዶር ፏፏቴ ጎራ በማለት ነው።
በፏፏቴው ቅጥር ግቢ ሻይ ቡና ወይም ቀዝቃዛ መጠጥ እንዲሁም ምግብ ከፈለጉ በማኀበር የተደራጁ ወጣቶች ያቋቋሙት የመዝናኛ ክበብ ይገኛል። ከርቀት የመጡ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ጎብኝዎች በዶንዶር ፏፏቴ ሲዝናኑ ውለው ማደር ቢፈልጉ በከተማዋ ውብ የእንግዳ ማረፊያዎችን በቀላሉ ማግኘት ይችላሉ።
በሙሉጌታ ሙጨ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!