ባሕር ዳር: ሚያዚያ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ጥንታዊቷ እና ታሪካዊቷ ደብረ ታቦር ስያሜዋን ያገኘችው በ1327 ዓ.ም በአጼ ሰይፈ አርዕድ ዘመነ መንግሥት ነው።
ከስያሜው ጋር በተያያዘ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ በተለይም ለመንፈሳዊ ተልእኮ ወደ እየሩሳሌም ይመላለሱ በነበሩ አባቶች በእየሩሳሌም ይገኝ ከነበረው የታቦር ተራራ ወይም ደብረታቦር ጋር በነበረው የተፈጥሮ የአቀማመጥ መመሳሰል ምክንያት እና በሌሎች መንፈሳዊ ጉዳዮች ደብር ኢየሱስ በሚለው ላይ ታቦር የሚለውን በማካተት ደብረታቦር ኢየሱስ ቤተክርስቲያን በሚል መጠራት ሲጀመር በዙሪያው ለተመሰረተው የመኖሪያ አካባቢም ደብረታቦር የሚለው አሁን ድረስ የከተማዋ መጠሪያ ሁኖ እንዲዘልቅ ምክንያት ሁኗል።
ደብረታቦር ማለት የቃሉ ትርጉሙም ደብረ ማለት ተራራ ሲሆን ታቦር ደግሞ ብርሃን በጥቅሉም የብርሃን ተራራ ማለት ነው። የደብረታቦር ከተማ ከ13ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ለነገሥታት መቀመጫነት ተመራጭ ካደረጓት ዋነኛ ጉዳዮች ውስጥ ከተማዋ እና አካባቢው የነበራቸው ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ወሳኝ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታዎች ይጠቀሳሉ። በሀገሪቱ ታሪክ ወታደራዊ እና አሥተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ታሪካዊ ድርሻ እንድታበረክትም አስችሏታል።
ለከተማዋ መሰረት ከጣሉት አጼ ሰይፈ አርዕድ ዘመን ጀምሮ በመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ በዋና የሀገር መዲናነት ተመራጭ የነበረች ከተማ ናት።
በተለይ በአካባቢው ለጤና ተስማሚ የአየር ንብረት መኖር በአጼ ሱስኒዮስ ዘመነ መንግሥትም ተመራጭ እንድትሆን አድርጓታል። በመሆኑም በደብረታቦር ከተማ አካባቢ አሪንጎ በሚባል ስፍራ በአጼ ሱስንዮስ የተጀመረው አሥተዳደራዊ ማእከልነት ትልቅ የሥልጣኔ አሻራ የተጣለበት ነበር።
የደብረታቦር ከተማ በኢትዮጵያ ታሪክ ዘመነ መሳፍንት በመባል በሚታወቀው ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ሰባዎቹ
እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ ለተመሰረተው እና በወቅቱ የፓለቲካ እና ወታደራዊ የበላይነት ለነበረው አሥተዳደር ዋነኛ ተመራጭ ከተማ ነበረች። በዚህ የታሪክ ወቅት የደብረታቦር ከተማ ምንም እንኳን የተጠናከረ ማእከላዊ መንግሥት በመላ ሀገሪቱ ባይኖርም መቀመጫቸውን በከተማዋ ያደረጉት መሳፍንቶች ጠንካራ አሥተዳደራዊ ሥርዓት የነበራቸው ናቸው።
ከ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ በኢትዮጵያ ታሪክ በዘመኑ ከፍተኛ ድርሻ የነበራቸው ወሳኝ ታሪካዊ ክንዋኔዎችን በማስተናገዱ በኩል የደብረታቦር ከተማ ቅድሚያውን ትወስዳለች። ለዚህም በኢትዮጵያ ዘመነ መሳፍንት ሲያከትም እና ወደ ማዕከላዊ መንግሥት ምስረታ ሽግግር ታሪካዊ ሂደት ቀዳሚ ጉዞውን ሲጀምር ደብረታቦር መንደርደሪያ ነበረች። ይህ የሽግግሯ ታሪካዊ ጉዞ በሁለት ዋነኛ ታላላቅ ተግባራት ሲንፀባረቅ መነሻው ደብረታቦር ከተማ ነበረች። እነዚህም በአጼ ቴዎድሮስ መሪነት የተካሄዱት አንደኛው የማዕከላዊ መንግሥት ዳግም ምስረታ ታሪካዊ ድል ሲሆን ሌላው እና ሁለተኛው በኢትዮጵያ ታሪክ ግንባር ቀደም የሆነው እና በደብረታቦር አካባቢ ጋፋት ላይ ተመስርቶ የነበረው የኢንዱስትሪ መንደር ተጠቃሽ ነው።
የደብረታቦር ከተማ በዘመኑ ለነበረው የሀገሪቱ ግዛት ክልል የማዕከላዊነት ድርሻዋ በወቅቱ ይካሄድ ለነበረው ወታደራዊ ዘመቻዎች መነሻ እና መንደርደሪያ በመሆን ከየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ የጎላ ሚና ነበራት። ከአጼ ቴዎድሮስ በኃላም የመጡት አጼ ዮሐንስ አራተኛ በአብዛኛው የማዕከላዊ መንግሥት ምስረታ እና ሌሎች ዘመቻዎችን ለማካሄድ ለአሥተዳደራዊ አመራራቸው የመረጧት እና ቤተ-መንግሥታቸውን በመሥራት መቀመጫቸውን ያደረጉት ደብረታቦር ከተማ ነበር።
በወቅቱ በጌምድር በመባል በሚታወቀው ሰፊ አሥተዳደር አካባቢ በበላይነት የተቀመጡት አሥተዳዳሪ ራስ ጉግሳ መቀመጫቸው በደብረታቦር ከተማ የነበረ ሲሆን ራስ ጉግሳ እና ደብረታቦር በዘመኑ ማዕከላዊ መንግሥት በበላይነት ለመቆጣጠር በነበረው የራሶች እና ባላባቶች ሽኩቻ ዋነኛ ዕእከል የነበሩ መሆናቸው ይታወቃል።
በደብረታቦር ከተማ የሀገር ጎብኝዎችን ትኩረት የሚስቡ በርካታ ታሪካዊ ቋሚ እና ተንቀሳቃሽ መስህብ ሀብቶች ይገኛሉ። ከእነዚህም በታሪካዊ ቅደም ተከተል በ1327 ዓ.ም የተመሰረተው የደብረታቦር ኢየሱስ ቤተክርስትያን ልዩ ጥበብ የሚስተዋልበት፣ በርካታ ቅርሶችም የሚገኙበት ነው።
ከከተማዋ አቅራቢያ የሚገኘው እና በ17ኛው ክፍለ ዘመን እንደተመሰረተ የሚነገርለት የአጼ ሱስንዮስ ቤተ መንግሥት ሕንፃ ቅሪት፣ በዚሁ ዘመናት በአካባቢው የተተከሉት የተለያዩ ጥንታዊ አብያተ ክርስቲያናት፣ ጋፋት የኢንዱስትሪ መንደር የነበረው እና አጼ ቴዎድሮስ ሴባስቶፓልን ያሠሩበት ታሪካዊ ስፍራ፣ የአጼ ዮሐንስ አራተኛ ቤተ-መንግሥት የነበረው ሕንፃ ቅሪትን ያሠሩት የኅሩይ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን ከእነ ቅርሶቹ፣ በወቅቱ አጼ ዮሐንስ ይጠቀሙበት የነበረው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ፣ ወንበራቸው፣ የገብርዬ ጦር እና የመሳሰሉት ይገኙበታል። በከተማዋ በኢትዮጵያ ብቸኛው የተክሌ አቋቋም የዜማ ማስመስከሪያ ዩኒቨርስቲ ይገኛል።
ከላይ ጉና ከታች ጣና የከተማዋን የአየር ንብረት የተመቻቸ አድርገውታል። በአጠቃላይ የደብረታቦር ከተማ ለወደፊቱ ለከተማዋ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችሉ የታሪካዊ መስህብ ባለቤት ናት። መረጃው የደብረታቦር ኮሙኒኬሽን ነው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!