ትስኪ ፏፏቴ – ከመስህብነት ባሻገር!

0
428

ባሕር ዳር: ሚያዚያ 04/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ትስኪ ፏፏቴ በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ውስጥ ከዳንግላ ከተማ በ38 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። ፏፏቴውን ለመጎብኘት ሁለት የመንገድ አማራጮችን መጠቀም ይቻላል። የመጀመሪያው እና በበጋ ወቅት ተመራጭ የኾነው ከዳንግላ ከተማ ተነስቶ በመኪና መጓዝ ነው።

በክረምት ወራት ግን በዚህ መስመር መጓዝ የሚቻለው 21 ኪሎ ሜትር ድረስ ብቻ ነው። ቀሪውን መንገድ በእግር ወይም በፈረስ መጓዝ ግድ ይላል። ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ ከብሔረሰብ አሥተዳደሩ ርእሰ ከተማ እንጅባራ በመነሳት ወደ መተከል በሚያመራው መንገድ እስከ ቅዳማጃ ከተማ ድረስ ከተጓዙ በኋላ በሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ ታጥፈው 16 ኪሎ ሜትር በመጓዝ ትስኪ ፏፏቴ መድረስ ይቻላል።

ሁለተኛው አማራጭ በበጋ ወቅት ከኾነ ልክ እንደ መጀመሪያው ኹሉ በመኪና ተጉዞ መድረስ ይቻላል። በክረምት ወራት ግን ፏፏቴው ላይ ለመድረስ 16 ኪሎ ሜትር ሲቀርዎት በእግር ወይም በፈረስ መጓዝ ግድ ይለዎታል። ትስኪ ፏፏቴን የሚፈጥሩት “አዊሲ” እና “ግዛኒ” የተባሉ ሁለት ትልልቅ ወንዞች ናቸው። እነዚህ ወንዞች ከየሚመነጩበት ሥፍራ ተነስተው ረጅም ርቀት ሳይገናኙ ከፈሰሱ በኋላ አፋፉ ላይ አንድ ላይ ይገናኛሉ። ከዚያም ጥልቅ ወደኾነ ገደላማ ሥፍራ እየተገማሸሩ ሲወርዱ የትስኪን ፏፏቴ ይፈጥራሉ።

ፏፏቴው ነጎድጓዳዊ ድምጽ ከመፍጠሩ ባለፈ የሚረጨው ውሃ አካባቢው በነጭ ጉም እንደዲሸፈን ያደርገዋል። በፏፏቴው ቀጣና አካባቢ ኾነው ቀና ሲሉ በፏፏቴው የሚፈጠረው ባለኅብረ ቀለም የቀስተ ዳመና መቀነት መሰል ምስል ለመንፈስ ሐሴትን ከማላበሱ ባለፈ የጎብኝዎችን ቀልብ ማርኮ የማቆየት ኃይሉ ከፍተኛ ነው።

ከትስኪ ፏፏቴ ፊት ለፊት ደግሞ በእድሜ ጠገብ ዛፍ የተሸፈነ ሸለቆ ይገኛል። በውስጡም የተለያዩ ብርቅዬ የዱር እንስሳት ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከልም ሰሳ፣ የምኒሊክ ድኩላ፣ ጦጣ፣ ጉሬዛ፣ ዠንጀሮ፣ ጥርኝ፣ ቀይ ቀበሮ እና ሌሎችን መጥቀስ ይቻላል።

ከትስኪ ፏፏቴ በቅርብ ርቀት የሚገኘውን የጥምብል ወንዝን በማገናኘት እና የፏፏቴውን ኃይል በመጨመር ፏፏቴው በተፈጥሮ ከሚሰጠው ጥቅም ባሻገር የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨትም እንደሚቻል በመስኩ ምርምር ያደረጉ ምሁራን ጠቁመዋል። እንደ ምሁራኑ ምክረ ሐሳብ ከፏፏቴው 75 ሜጋ ዋት ያህል ኤሌክትሪክ ማመንጨት ይቻላል። የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ድረ ገጽ እንዲሁም የቱሪስት መስህብ ሐብቶች መጽሐፍን በመረጃ ምንጭነት ተጠቅመናል።

በሙሉጌታ ሙጨ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here