“ጎብኚ የናፈቀው የውበት ሰገነት”

0
228

ባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 12/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ተፈጥሮ ውብ አድርጎ ሞሽሮታል፤ ከታላቋ ሀገር ከኢትዮጵያ ተራራዎች ሁሉ ከፍ አድርጎ ፈጥሮታል፤ ታይቶ የማይጠገብ ውበትን አድሎታል፤ አምሳያ የሌለው ውበት ያለበት፣ ያዩት ሁሉ እንደ አዲስ የሚናፍቁት፣ የሚጓጉለት ነው፡፡
እጆች ሁሉ ቢጽፉለት የሚመኙለት፣ ብርቅ የኾኑ እንስሳት የሚኖሩበት፣ ከውበት ላይ ውበት የተደረበለት ድንቅ ስፍራ ነው፡፡

የዓለም ጎብኚዎች ሁሉ ኢትዮጵያን ለማየት ከሚጓጉላቸው ውብ የተፈጥሮ ሥፍራዎች በቀዳሚነት ይጠቀሳል፤ ሁሉም የውበት ሰገነት የኾነውን የስሜን ተራራዎችን ማየት ይፈልጋል፡፡ ይህ የውበት ሰገነት በተፈጥሮ እና በሰው ሠራሽ ችግሮች ምክንያት ጎብኚዎች ርቀውታል፤ እርሱም ናፍቋቸዋል፤ እነርሱም ናፍቀውታል፡፡ ጎብኚዎች መቅረታቸውን ተከትሎ ቱሪዝሙ ተጎድቷል፡፡ ቱሪዝሙ በመጎዳቱ ገቢያቸው በቱሪዝም የተመሠረተ ወገኖች ተጎድተዋል፡፡

በስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የዋልያ አስጎኚ ማኅበር ሊቀ መንበር ካሳ ብርሃኔ ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና ከጦርነቱ አስቀድሞ ወደ ስሜን ተራራዎች የሚመጡ ጎብኚዎች ቁጥር ብዙ ነበር ፡፡ ጎብኚዎች በስፋት ስለሚመጡ አስጎብኚዎች፣ ባለሆቴሎች፣ ባሕላዊ መጓጓዣ አቅራቢዎች በአጠቃላይ የአካባቢው ማኅበሰረብ ተጠቃሚ ነበር ይላሉ፡፡

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ የሰሜኑ ጦርነት እና አሁን ያለው የአማራ ክልል የፀጥታ ሁኔታ ጎብኚዎች የማይለዩትን አካባቢ ሰው እራበው፡፡ ይሄም በቱሪዝም ገቢ ላይ ሕይወታቸውን የመሠረቱ ወገኖችን በእጅጉ ጎዳቸው፡፡ እንደ ሊቀመንበሩ ገለጻ በቱሪዝሙ መቀዝቀዝ ምክንያት በሥነ ልቦና፣ በምጣኔ ሃብት፣ በማኅበራዊ ግንኙነት በእጅጉ ተጎድተናል ነው ያሉት፡፡ በተለይም ይላሉ ሊቀመንበሩ የደረሰብን የምጣኔ ሃብት ጉዳት ከመግለጽ በላይ ነው፡፡

የቱሪዝም እቅስቃሴው በመቀዛቀዙ ላለፉት ዓመታት ከሥራ ውጭ ኾነናል፤ አብዛኛዎቻችን ቤተሰብ እንመራለን፣ ልጆች እናሳድጋለን፤ አሁን ግን ገቢያችንን አጥተናል፤ አንድ የመንግሥት ሠራተኛ የአንድ ወር ደመወዙ ቢቀር ምን ያክል ሕይወቱ እንደሚቃወስ አስበው? እኛ ግን ለወራት አይደለም፣ ለዓመታት ነው ገቢ ያጣነው፣ ያለ ምንም ገቢ መቅረት ደግሞ ተጽዕኖው ከፍ ያለ ነው ይላሉ፡፡

ለወትሮው አስጎብኚ የሀገር አምባሳደር ነው የሚሉት ሊቀመንበሩ አሁን ግን በርካታ አስጎብኚዎች ተበትነዋል፤ አካባቢውን ለቀው የወጡ አሉ፤ የቀን ሥራ የሚሠሩ አሉ፤ ጉዳታችን እጅግ ከባድ ነው ብለዋል፡፡ እኛ ብቸኛ ገቢያችን ቱሪዝም ነው፣ ቱሪዝም ሲቆም የእኛ ገቢም ቆሟል፤ ጉዳታችን ከመናገር፣ ከመግለጽ በላይ ነው ይላሉ፡፡ የሰላም እጦቱ የጎብኚዎችን ፍሰት አቆመ፣ የጎብኚዎች ፍሰት ሲያቆም ደግሞ ከቱሪዝም የሚገኘው ገቢ ቀረ፤ ከቱሪዝም የሚገኘው ገቢ ሲቀር ለፓርኩ ሲደረግ የነበረው እንክብካቤ ቀነሰ ነው የሚሉት፡፡

የሰላም እጦቱ ፓርኩ ላይ አደጋ እንዲበዛበት አድርጓል፤ ብርቅዬ እንስሳት እንክብካቤ እንዳያገኙ፣ ጥቃት እንዲደርስባቸው እያደረገ ነው ይላሉ፡፡ የሰላም እጦቱ ከቱሪዝም ገቢ የሚያገኘውን የአካባቢውን ማኅበረሰብ ብቻ ሳይኾን የፓርኩን ኅልውናም በእጅጉ የሚፈትን ነው ብለዋል፡፡

ሁሉም የሰላምን ትርጉም በትክክል ተረድቶ ለሰላም የሚከፈለውን ዋጋ መክፈል መቻል አለበት፤ መንግሥት ደግሞ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፤ በክልሉ የተፈጠረውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት፤ ቱሪዝም እንደ ብርጭቆ ነው፤ እንክብካቤ ይፈልጋል፤ ሰላም በሌለበት ስለ ቱሪዝም ማውራት አይቻልም ነው ያሉት፡፡ ሀገር በሰላም እጦት ምን ያክል ዋጋ እየከፈለች እንደኾነ መረዳት ይገባልም ብለዋል፡፡

የስሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት ተወካይ ኃላፊ ኤፍሬም ወንዴ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና የሰሜኑ ጦርነት ከመነሳቱ አስቀድሞ በዓመት እስከ 35 ሺህ የሚደርሱ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ይጎብኙት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ ከቱሪዝም ገቢ የሚያገኙ ወገኖች ተጠቃሚ እንደነበሩም ገልጸዋል፡፡ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ በሰሜኑ ጦርነት እና አሁን ባለው የአማራ ክልል የፀጥታ ችግር ምክንያት ቱሪዝሙ በእጅጉ አሽቆልቁሏል ነው ያሉት፡፡ የጎብኚዎች ቁጥርም በእጅጉ ማሽቆልቆሉን ነው የተናገሩት፡፡ ከቱሪዝም ዘርፉ ገቢ የሚያገኙ ወገኖች ተጎድተዋል ብለዋል፡፡

የቱሪዝም እንቅስቃሴው መዳከም ፓርኩን ለመጠበቅ በሚደረገው ሥራ አሉታዉ ተጽዕኖ እያሳደረ መምጣቱንም ተናግረዋል፡፡ ከቱሪዝም የሚገኘው ገቢ ሲቀንስ ፓርኩ ላይ ጥቃት የሚያደርሱ ሰዎች እንዲፈጠሩ እንዳደረገውም አንስተዋል፡፡ በተደጋጋሚ የሚነሳ የእሳት ቃጠሎ ሙከራዎችን መቆጣጠር የሚያስችል ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የእሳት ቃጠሎ በተነሳ ጊዜም በርብርብ ለመቆጣጠር የሚያስችል መዋቅር መዘርጋቱንም አንስተዋል፡፡ ፓርኩን መጠበቅ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

የሰሜን ጎንደር ዞን ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ኀላፊ አስራት ክብረት እየተፈጠሩ ያሉ ተደጋጋሚ ችግሮች ቱሪዝሙ በሚፈለገው ልክ እንዳያድግ አድርገውታል ነው ያሉት፡፡ በዞኑ ሰላም በመኖሩ መጠነኛ የጎብኚዎች እንቅስቃሴ መኖሩን ያነሱት ወይዘሮ አስራት የጎብኚዎች ፍሰት በሚፈለገው ልክ አይደለም ብለዋል፡፡ ዞኑ ብቻ ሳይኾን በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ሰላም ኾኖ የቱሪዝም እንቅስቃሴው እንዲነቃቃ ይፈልጋል ነው ያሉት፡፡

በቱሪዝሙ መቀዛቀዝ ምክንያት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እና ገቢያቸውን በቱሪዝም እንቅስቃሴ ያደረጉ ወገኖች በከፋ ችግር ውስጥ ናቸው ብለዋል፡፡ የቱሪዝም እንቅስቃሴው ሲቆም አስጎብኚዎች ለችግር ተጋልጠዋል ያሉት ኀላፊዋ ለአስጎብኚዎቹ ድጋፍ ለማድረግ ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል፡፡ በቂ ድጋፍ ባይኾንም የዕለት ጉርስ የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸት ሰርተናል ነው ያሉት፡፡ የቱሪዝሙ እንቅስቃሴ እስኪመለስ ድረስ የሥራ እድል ተፈጥሮላቸው ሕይወታቸውን መምራት እንዲችሉ ለማድረግ ያደረጉት ጥረት አለመሳካቱንም ተናግረዋል፡፡ አሁንም ፕሮጄክቶችን በመቅረጽ ድጋፍ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ትልቁ መፍትሔ ሰላምን በማረጋገጥ የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ወደነበረበት መመለስ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ አሁን ላይ ሙሉ ለሙሉም ባይኾን እንግዶች እየመጡ የቱሪዝም እንቅስቃሴ መጀመሩንም አንስተዋል፡፡ ፓርኩ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ ሥራ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ፓርኩ ሲኖር ማኅበረሰቡ ይጠቀማል ያሉት ኀላፊዋ ማኅበረሰቡ ፓርኩን እንዲጠብቅ እና ተጠቃሚነቱን እንዲያሳድግ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡ ፓርኩ የሀገር ሃብት በመኾኑ መልማት እና መጠበቅ አለበት ነው ያሉት፡፡ በፓርኩ ላይ ጥፋት የሚፈጥሩ አካላትም ተጠያቂነት ይኖራል ብለዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here