ገታ መስጂድ – የእሥልምና አስተምህሮ ቅርስ

0
291

ባሕር ዳር: ግንቦት 19/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ገታ መሥጂድ በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ 06 ቀበሌ የሚገኝ ሃይማኖታዊ ስፍራ ነው። መሥጂዱ የነቢዩ ሙሐመድ (ሰለሏሁ ዐለይሂ ወሰለም) የዘር ሀረግ እንዳላቸው በሚታመንባቸው በሃጂ ቡሽራ አማካይነት በ1790 ዓ.ም አካባቢ እንደተመሠረተ ይነገራል።

ከኮምቦልቻ ወደ አዲስ አበባ በሚያስኬደው የአስፋልት መንገድ 16 ኪሎ ሜትር ተጉዘው ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ በመታጠፍ የ4 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ከተጓዙ በኋላ ያገኙታል፡፡ ኢማም ሙህዲን ሃጂ አሕመድ ሙሐመድ ወሌ ሰጊድ ቡሽራ (የሃጂ ቡሽራ 5ኛ ትውልድ) እና የመስጂዱ አስጎብኚ በመስጊዱ ሃጂ ቡሽራ የከተቧቸው 500 የሚኾኑ የእሥልምና መጻሕፍት መኖራቸው ገልጸዋል።

12 ሺህ የሚኾኑ ደረሣዎች እና ኢስላማዊ ምሁራንም ተምረውበት በተለያዩ ቦታዎች የሚያስተምሩ ዓሊሞችን ያፈራ በመኾኑ መስጂዱን ልዩ ያደርገዋል። የሃጂ ቡሽራ ሰይፍ እና ሙስብሃቸውም አሁን ድረስ በመስጂዱ መኖሩን የቱሪስት መስህብነቱን ጨምሮለታል። የሃጂ ቡሽራ ገታ መስጂድ የእስልምና አስተምህሮ መስጫ እና ለሀገር ዱዓ የሚደረግበት ነው። በየዓመቱ የመውሊድ ዕለትም ከሀገር ውስጥም ከውጪም ቱሪስቶች እየመጡ ይጎበኙታል።

ገታ መስጂድ መብራት፣ ውኃ እና መንገድ ያለው ሲኾን የእንግዳ መቀበያም እንደተዘጋጀለት ኢማም ሙህዲን ገልጸዋል። በቃሉ ወረዳ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቱሪዝም መዳረሻ ልማት ባለሙያ አወል መሐመድ ከነቢዩ ሙሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ጋር የዘር ሃረግ እንዳላቸው የሚታመንባቸው ሃጂ ቡሽራ የመሠረቱት ገታ መስጂድ ረጂም እድሜ ያለው፣ መሥራቹ እሥልምናን በማስተማር የኖሩበት እና በመውሊድ በዓል በብዛት የሚከበርበት መኾኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል። ሃጂ ቡሽራ ወልይነት ጭምር እንዳላቸው የሚታመንባቸው ታላቅ አባት እንደነበሩም ባለሙያው አክለዋል።

በበዓል ወቅት በርካታ ሙስሊሞች የሚታደሙበት መስጂዱ ሃጂ ቡሽራ በውጪ እስላማዊ ሀገራት በተዘዋወሩ ጊዜ ያመጧቸው ጎራዴዎች፣ የጻፏቸው መጻሕፍት፣ ይገለገሉባቸው የነበሩ ቁሶች ይገኙበታል። የሚዲያ ተቋማት እና ተመራማሪዎችን የሚስብ መኾኑም ነው የተገለጸው። በመውሊድ ዕለት ጎብኚው ሳይቸገር እንዲቆይ ወረዳው አስፈላጊውን ዝግጅት አድርጎ እንደሚሠራ ነው አቶ አወል መሐመድ የጠቀሱት።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here