የጮቄ ተራራዎች “የኢትዮጵያ የውኃ ቋት”

0
463

ባሕር ዳር፡ ግንቦት 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የጮቄ ሰንሰለታማ ተራራ የሚገኘው በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ነው፡፡ ይህ ድንቅ ሥፍራ “የኢትዮጵያ የውኃ ቋት” በመባልም ይጠራል፡፡ ከፍታው ደግሞ 4 ሺህ 100 ሜትር ነው። በከፍታ ረገድ በሀገር አቀፍ ደረጃ አራተኛ ነው፡፡ ይህ የውኃ ቋት 53 ሺህ 558 ሄክታር መሬትን ይሸፍናል፡፡

የጮቄ ሰንሰለታማ ተራራ በዋናነት ስናን ፣ ደባይ ጥላት ግን ፣ ሰዴ ፣ ቢቡኝ እና ማቻከል ወረዳዎችን ያካልላል፡፡ ሰፊውን ቦታ የሚሸፍነው ግን የስናን ወረዳ ነው፡፡ የተወሰኑ ምዕራብ ጐጃም ወረዳዎችም በጮቄ ቀጣና ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ከደኅንነት ጋር በተገናኘ ስማቸውን እንዳንጠቀም የጠየቁን ከደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ሰጫችን ጮቄ ኢትዮጵያን የውኃ ማማ እና የከፍታ ጣሪያ በማስባል ግንባር ቀደም ነው ይላሉ፡፡ “ለምን?” ቢሉ 273 ትናንሽ ጅረቶች እና 23 ትላልቅ ወንዞች መነሻቸው ከጮቄ ሰንሰለታማ ተራራ ነው ባይ ናቸው። መረጃ ሰጫችን በተለይ በክረምት ወራት ለተወሰኑ ሳምንታት በበረዶ ተሸፍኖ ይቆያል፤ ከዚህ በተጨማሪም በበጋ ወቅት በተወሰኑ ወራት በረዶ አይጠፋበትም፡፡

ከጮቄ ተራራ የሚንፏለሉት ፏፏቴዎች በአፍሪካ ብሎም በዓለም ስሙ ለገነነው የዓባይ ወንዝ ኹነኛ ገባሮች ናቸው። የዓባይ ውኃ ወደ 10 በመቶው በእነዚህ ጅረት እና ወንዞች አማካኝነት ከጮቄ ተቀድቶ የሚሞላ ስለመኾኑም ይገልጻሉ። ጮቄ እጹብድንቅ ነው፤ ይህን ውበቱን ዓለም መስክሮለታል። በመኾኑም በጮቄ ድንቅ ሥፍራ ጉያ የሚገኘው “የጮቄ ቱሪዝም መንደር” በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት የ2022 የዓለም ምርጥ የቱሪዝም መንደር ተብሎ ዕውቅና ተሰጥቶታል ብለውናል፡፡

ጮቄ በተፈጥሯዊ ገጽታውም ተፈጥሮ ውበቷን ሳትሰስት ያፈሰሰችለት በጣም ሳቢና መንፈስን የሚያረካ የተፈጥሮ ገፀ-በረከት ነው ባይ ናቸው፡፡ አካባቢው በብዝኃ ሕይወትም የታደለ ነው፡፡ አካባቢው በበርካታ ሀገር በቀል እፅዋት የተሸፈነም ነው ብለዋል፡፡ በተራራው ላይ እንደ አስታ፣ ጅባራ ፣ ግምይ፣ ጽድ ፣ ኮሶ፣ ኮሸሽሌ ፣ አይዳኝ፣ ቀጋ እና አሸንግድዬ የመሳሰሉት ዕፅዋት ይገኙበታል፡፡

በጮቄ ቀጣና ከ16 በላይ አጥቢ የዱር እንስሳት እንዳሉም መረጃ ሰጫችን ተናግረዋል፡፡ ለአብነት:-ነብር ፣ ቀበሮ ፣ ድኩላ ፣ጉሬዛ ፣ ሚዳቋ ፣ ጅብ ፣ ዝንጀሮ ፣ የዱር አሳማ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ከ41 በላይ የአዕዋፍት ዝርያዎችም ይገኛሉ፡፡ ቅልጥም ሰባሪ የሚባለው ብርቅየ ወፍም መገኛው ጮቄ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ጮቄ በውስጡ አካቶ ከያዛቸው መልከዓ-ምድራዊ አቀማመጥ ውስጥ “አራት መከራከር” የሚባለው ሥፍራ አንደኛው ነው፡፡ ይህ ተራራ በስናን ወረዳ ዋና ከተማ ከረቡዕ ገበያ በ1ዐ ኪሎ ሜትር ሰሜን ምዕራብ ርቀት አካባቢ ይገኛል፡፡ ጮቄን እንዴት መጎብኘት ይቻላል? ከምሥራቅ ጎጃም ባሕልና ቱሪዝም መምሪያ ባገኘነው መረጃ ወደ ተራራው ለመሄድ ከደብረ ማርቆስ ድጎ መስመር ከተጓዙ በኋላ “ጠጠር” ከሚባል ቦታ በመውረድ ከቦታው መድረስ ይቻላል፡፡

የጮቄን ተራራዎች ከደብረ ማርቆስ – ድጐ-ጽዮን -ሞጣ የሚወስደው የጠጠር መንገድ ያዋስነዋል፡፡ ከድጐ-ጽዮን- ፈረስ ቤት ፣ ከደብረማርቆስ ቁይ ፣ ቢቸና የሚያገናኙ አውራ መንገዶችም የሚያቋርጡት በመኾኑ ጮቄን ለመጐብኘት የመንገድ ችግር የለበትም፡፡ በተለይም ከደብረማርቆስ – ድጐ-ጽዮን ያለው አውራ መንገድ የአካባቢውን ከፍተኛ ቦታዎች አቋርጦ ስለሚሄድ ቦታውን ለመጐብኘት እንደ አንድ ዕድል ሊወሰድ ይችላል፡፡

ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በድረ ገጹ እንዳሰፈረው ዩኒቨርሲቲው የጮቄ ተፋሰስ ምርምር እና ልማት ፕሮጀክት አቋቁሞ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል፡፡ በዚህም መሰረት ዩኒቨርሲቲው የጮቄን ችግሮች በምርምር በመፍታት እና ለማኅበረሰቡ ዕውቀት በማካፈል እያገዘ ስለመኾኑም መረጃ ሰጫችን ነግረውናል፡፡

የጮቄ ቀጣና ስድስቱ አዋሳኝ ወረዳዎችን አካቷል፡፡ እንደ ማሳያ በሰዴ፣ ደባይ ጥላት ግን እና በቢቡኝ ወረዳዎች ከ1 ሺህ በላይ ወጣቶችን በንብ ማነብ ሥራ እንዲሰማሩ አድርጓል፡፡ በዚህም ከከብት ርባታ የበለጠ በንብ ማነብ መሰማራታቸው ጥቅም እንዲያገኙበት እንዳደረጋቸው ነው የሚገልጹት፡፡
ይህንን አይነት አማራጭ የኢኮኖሚ ምንጭ በሁሉም የጮቄ አዋሳኝ ወረዳዎች በማስፋት አርሶ አደሩ በጮቄ ላይ የሚያደርሰውን ልቅ ግጦሽ በዘላቂነት የመከላከል ሥራ በትኩረት እንደሚከናውንም ነው ያብራሩት፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here