ባሕር ዳር: ግንቦት 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በቅሎ አግቱ ጨጨሆ መድኃኔዓለም ገዳም በደቡብ ጎንደር ዞን በላይ ጋይንት ወረዳ ቀበሌ 19 ወይም ጨጨሆ ተብሎ በሚጠራ ቀበሌ ውስጥ ይገኛል። ከባሕር ዳር ወልድያ በሚወስደው የአስፋልት መንገድ 195 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። በደቡብ ጎንደር እና በሰሜን ወሎ ዞኖች መዋሰኛ ላይ የሚገኝ በተፈጥሮ ደን የታጀበ ገዳም ነው።
በላይ ጋይንት ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ እንደሻው ሽፈራው በቅሎ አግቱ ጨጨሆ መድሐኔያለም ቤተክርስቲያን በ5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአጼ ካሌብ የንግሥና ዘመን እንደተመሠረተ የታሪክ ድርሳናትን ዋቢ አድረገው ይገልፃሉ። በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት እና ትውፊት መሠረትም በርካታ ተዓምራትን እንደሠራም ይነገርለታል። የጎንደሩ ንጉሥ አጼ በካፋ ስለታቸው በመድረሱ የእጅ ሥራ ድንኳን ማስገባታቸውም ይጠቀሳል ብለዋል።
አጼ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን አንድ በማድረግ ውጥናቸው ለሰባት ቀናት ሱባኤ እንደገቡበት ይነገራል። ከወሎዋ ንግሥት ወርቂቱ ጋር የነበራቸውን አለመግባባት ለመፍታት ወደ ወሎ ሲሄዱም ከነሠራዊታቸው በሰላም ከተመለሱ በቅሏቸውን ከነሙሉ ዕቃዋ እንደሚሰጡ ቃል ገቡ (ተሳሉ)። ስዕለታቸው ሰምሮ በሰላም ሲመለሱ በበቅሎዋ ምትክ ገንዘብ ሰጡ። ይኹንና በቅሎዋ ከዚያ ቦታ መንቀሳቀስ ስላልቻለች ”በቅሎ አግቱ መድኃኔለም” ብለው እንደሰየሙት ይነገራል። ከዚያ ወዲህም ‘በቅሎ አግቱ ጨጨሆ መድኃኔዓለም’ ተብሎ ይጠራል ያሉት አቶ እንደሻው አጼ ቴዎድሮስን ጨምሮ የተለያዩ ንጉሦች እና ባላባቶች የመስቀል፣ አክሊል፣ መቋሚያ እና ሌሎች ስጦታዎችን እንዳበረከቱለት አብራርተዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ግማደ መስቀል ከኢየሩሳሌም ወደ ግሼን ደብረ ከርቤ ሲጓዝም በዚሁ ቦታ አርፎ ለሦስት ቀናት መቆየቱንም ይነገራል። ከግማደ መስቀሉ ጋር የመጡ የወርቅ መስቀል እና ጽዋም ይገኙበታል። ጨጨሆ መድኃኔዓለም አሁን ድረስ መስማማት ያልቻሉ ሰዎች ተፈራርመው ወደ ገዳሙ በመሄድ ችግራቸውን እንደሚፈቱም ይነገራል።
አካባቢው ጨጨሆ የተባለበት ምክንያት በዘመነ አጸባ (በክፉ ዘመን) ሕዝቡ በረሃብ እና በበሽታ በማለቁ ሁለት ቄሶች ብቻ ቀርተው በጥምቀት በዓል ታቦቱን ተሸክመው ለማክበር የሚያጅባቸው እንደሌለ አስበው ሲጨነቁ የእግዚአብሔር መላዕክ ታቦቱን ይዘው እንዲወርዱ ማዘዙን እና ከእግዚአብሔር የታዘዙ ነጫጭ ዝንጀሮዎች ታቦቱን አጅበው አውርደው መልሰው እንዳስገቡት ይነገራል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ታቦቱ ‘ዝንጀሮ አስጨብጭብ’ ተብሎ መጠራቱን እና በሂደትም ጨጨሆ የሚለው ስያሜ እንደጎላና የአካባቢው መጠሪያ እንደኾነም ይነገራል።
በገዳሙ ዙሪያ የተፈለፈሉ ዋሻዎች ተጨማሪ መስህብ ኾነውታል። ዋሻዎቹን በሰሜን ወሎዋ ጎረጎር ማርያም ገዳም ሲጸልዩ የነበሩበት አባ ገብረሥላሴ ደፋር ተሰማ የተባሉ መነኩሴ በ1983 ዓ.ም ከአለት ፈልፍለው ሠርተዋቸዋል። ባለ አምስት እና ባለ ሰባት ምሰሶዎችም ናቸው። ፍልፍል ዋሻዎቹ አራት ጽላት ማለትም የቅዱስ ገብርኤል፣ የበዓለ እግዚአብሔር፣ የኪዳነ ምህረት እና የቅዱስ ኡራኤል ጽላቶች ገብተውባቸዋል። አባ ገብረ ሥላሴ ደፋር ጸሎት የሚያደርሱበትም አንድ ፍልፍል ዋሻ ከአምባው አናት ላይ እንደሚገኝ በላይ ጋይንት ወረዳ ባሕልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን መሪ እንደሻው ሽፈራው ገልጸዋል።
በቅሎ አግቱ ጨጨሆ መድኃኔዓለም መጋቢት 27 ቀን ገዳሙ እና የአካባቢው ማኅበረሰብ የሚዘክረው ዓመታዊ ክብረ በዓል ያለው ሲኾን ጥቅምት 27 ቀንም ይከብራል። የገዳሙ ቤተ ክርስቲያን መንገድ ዳር ላይ በመኾኑ ከጎንደር ወደ ወሎ የሚመላለሱ የሃይማኖቱ ተከታይ ተጓዦችም ከመኪና እየወረዱ ይሳለማሉ፣ ይሳላሉ እንዲሁም ስዕለት ያስገባሉ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!