የላፁ አቡነ እዮብ ገዳምን በወፍ በረር!

0
261

ባሕር ዳር፡ ሰኔ 03/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከዋግ ኽምራ ዋና ከተማ ሰቆጣ በሥተ ሰሜን አቅጣጫ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል – የላፁ አቡነ እዮብ ገዳም፡፡ ይህን ገዳም ለማግኘት መነሻዎትን ሰቆጣ ከተማ አድርገው ስምንት ኪሎ ሜትር ርቀት ያህል እንደተጓዙ የላፁ አቡነ እዮብ ገዳምን ያገኙታል።

ወደ ገዳሙ በእግር፣ በጋማ ከብት እና በመኪና ( የተወሰነውን ርቀት) መሄድ ይቻላል። የላፁ አቡነ እዮብ ገዳምን በምዕራብ የማይጉንዶ ንዑስ ከተማ፣ በሰሜን የለዛ ማርያም ቤተ ክርስቲያን፣ በምሥራቅ የጥራሪ ወንዝ እንዲሁም በደቡብ የአኽተራ ማርያም ያዋስኑታል፡፡ ለላፁ አቡነ እዮብ ገዳም ኩታ ገጠም የኾነው የጥራሪ ወንዝ እና ተፋሰሱ ደግሞ ለዋግ ማኅበረሰብ እንዲሁም ብዝኃ ሕይዎቱ ስትንፋስ ነው። አካባቢው የአማዞን ጥቅጥቅ ደን ይመስላል።

ይህ እጹብ ድንቅ ገዳም የዋግ ኽምራ ይዞታ በኾነው የጥራሪ ወንዝ በምዕራብ በኩል እንደመከተሙ ዙሪያ ገባው ዓመቱን ሙሉ አረንጓዴ ልምላሜ በማይለየው ሀገር በቀል እድሜ ጠገብ ዛፎች የተከበበ ነው። የገዳሙን ደን መጠለያ ያደረጉ እንደ ሽመላ፣ ቆቅ፣ ጅግራ፣ የበረሃ ርግብ፣ መስቀሌ፣ ንሥር፣ ጉጉት፣ እርኩም የመሳሰሉ ብርቅዬ አእዋፍት ከትመውበታልና ነው።

የእጣን፣ የቅልጣ፣ የሙጫ፣ የብሳና፣ የላፍዲ እና የጠንበለል የዕፅዋት ዓይነቶችም በብዛት ይገኙበታል። ጥንጁት፣ አባሎ እና ወይራም እንዲሁ። ገዳሙ ዙሪያ ገባው በድንቅ ዋሻዎች የተከበበ ነው። በዋሻው ደግሞ መናንያን ጾሎት እያደረሱ ይኖሩበታል። በሰቆጣ ወረዳ ባሕል እና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የመስህብ ሥፍራዎች እና ቅርስ ጥበቃ ባለሙያ ደባሱ ሥዩም እንደገለጹት የላፁ እዮብ ገዳምን በስድስተኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አባ እዮብ የሚባሉ መናኝ አበደይረ ማርያም በሚባል ቦታ እንደመሰረቱት ተናግረዋል።

እንደ ባለሙያው ገለጻ የገዳሙ የአሠራር ጥበብ እጹብ ድንቅ የሚባል ዓይነት ነው። ለአብነት ቤተ መቅደሱ እና መንበሩ እርስ በርሳቸው ተያይዘው የተገነቡ ናቸው። ገዳሙ በወቅቱ የነበሩ አባቶች ለድንጋዩ ልዩ ቅርጽ አውጥተው፣ ጡቡን በእሳት ጠብሰው የገነቡት በመኾኑ ጥንካሬው የሚያወላዳ አልነበረም። የአሠራር ጥበቡም ዓይነ ገብ ነው።

ይህ ገዳም ለ350 ዓመታት ያክል በታላቁ አባት አቡነ እዮብ ሲገለገል ቆይቷል። ይሁን እና በ9ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዮዲት ጉዲት የቃጠሎ አደጋ አጋጥሞት እንደ ነበር ባለሙያው ተናግረዋል። በየጊዜው ወደ ላፁ አቡነ እዮብ ገዳም የሚሄደው አማኝ የትየለሌ እንደነበር የሀገር ጎብኝዎችም መዳረሻ እንደነበር ባለሙያው ነግረውናል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በስሜኑ ጦርነት እና አሁን ደግሞ ክልሉ ባጋጠመው የሰላም እጦት ምክንያት ወደ ላፁ አቡነ እዮብ ገዳም የሚሄደው አማኝ እና ጎብኝ እንደቀነሰ ባለሙያው ጠቁመዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here