ባሕር ዳር: ነሐሴ 01/2016 ዓ.ም (አሚኮ) አቶ ተመቸ ጠጌ በራያ የቆቦ ወረዳ ነዋሪ ናቸው፡፡ በሀገሬው ልማድ ቦርቀው፣ ላሎ ጉማ ጨፍረው፣ አግብተው እና ልጅ ወልደው ወግ ማዕረግ አይተዋል፡፡ ይሁን እና ከስድስት ዓመት በፊት ወንድማቸው በማኅበራዊ ግንኙነት በተፈጠረ ግጭት በእጃቸው የሰው ሕይዎት ጠፍቶባቸዋል።
‘ደም መቃባት’ ሲከሰት የሞቀ ቤት ይፈታል፤ ቀን በአደባባይ ማታ በእልፍኝ እንደልብ መኖር ያስቸግራል፡፡ የስጋት ደመና ያንዣብባል። ደም ሲቃቡ አደባባይ መዋል ቀርቶ ቤት ውስጥ መደበቅም ይከብዳልና ወገኑ ተጨነቀ። እነ አቶ ተመቸ ‘በሞቴ አፈር ስኾን’ ብለው ገልግለው ያበሉ ያጠጡበትን ቤት ለቅቀው ከነዘመዶቻቸው ተሰደዱ። ያጎረሱ እጆቻቸውም ለልመና ተዳረጉ።
ሀገሬውም በሰው ሕይዎት መጥፋትም ባንዣበበው መበቃቀልም ስጋት ገባው። ‘እግዚኦ!’ ተባለ፡፡ ሴቶች ‘እርፎ መረባ’ እያሉ ፈጣሪ ምሕረት እና እርቅ እንዲልክላቸው ተማጸኑ፡፡ ከተጋረጠባቸው አደጋ መውጫቸው ክሶ መታረቅ ብቻ ነበር እና እነ አቶ ተመቸ አስታርቁን ብለው ተማፀኑ። ውሎ ሲያድር የተናደደ ሲበርድ፣ ያዘነም ሲረጋጋ ‘ያለፈ አልፏልና ይቅር ተባባሉልን ደም ይድረቅ’ ተባለ። በራያ ምድር የተጣላን ማስታረቅ፣ የተጋደለን ደም ማድረቅ፣ ሽማግሌ እና ሽምግልና ሲታሰብ፤ ከተራራ የገዘፈ፣ ከተቋምም ያለፈ፣ ከባሕል፣ ከታሪክ እና ከሃይማኖት የተጋመደ በማኅበረሰቡ ስጋና ደም የተዋሃደ ተቋም አለ – ዘወልድ።
በቀል እንዳይኖር፣ ኅብረተሰቡ በግጭት እንዳይተላለቅ ከሚጠብቁ እሴቶች መካከልም አንዱ ነው። በወልድያ ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ ሳይንስ እና ሥነ ሰብዕ ኮሌጅ ዲን እና የፖለቲካ ሳይንስ መምህር በላይ አስማረ የዘወልድ የሽምግልና ሥርዓትን ሀገር በቀል ዕውቀት፣ የሰላም ግንባታ እና የማኅበረሰብ ግንኙነት ድልድይ ነው ሲሉ ይገልጹታል፡፡ ዘወልድ በሕይዎት ባይኖሩም የእርሳቸው መንፈስ አለ፤ በሽማግሌዎቹ ላይም ያድራል ተብሎ ስለሚታሰብ በማኅበረሰቡ ክብር እንዳለው ይገልጻሉ፡፡ በዘወልድ ሥርዓት አልታረቅም ማለት የለም፡፡ የማይታረቅ ከማኅበረሰቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎዎች ይታገዳል፤ ስለኾነም የሟች ወገን ‘ከአካባቢው ባሕል እና ከሀገር ሽማግሌ አንወጣም፤ እንምከር’ ይላል።
👉 የዘወልድ ምንነት እና ታሪክ
የዘወልድ የእርቅ ሥርዓት የተጀመረበት የተረጋገጠ ጊዜ ባይታወቅም ከ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ፍትሕ እንዳይጓደል ሲሠራ የቆየ ሥርዓት እንደነበረ ይጠቀሳል። የእርቅ ሥርዓቱ ዘወልድ፣ ሰንየሰገድ፣ መዛርድ እና ክፍሎ የሚባሉ የዘወልድ አሳኖ ልጆች በወቅቱ ራያ ተብሎ የሚታወቀውን አካባቢ ተከፋፍለው ያሥተዳድሩ በነበረ ጊዜ የግጭት አፈታት እና የእርቅ ሥነ ሥርዓታቸው እንደኾነ ነው የሚታወቀው። አሁን ላይም ሥነ ምግባራቸው የተሻሉ እና በማኅበረሰቡ ተቀባይነት ያላቸው አባቶች እየተመረጡ ባሕሉ ቀጥሏል፡፡ በራያ ወረዳ የዘወልድ ሽማግሌ አቶ ፈንታ ጫኔ ‘‘ቄሶች መስቀል ይዘው ዱበርቲው እርፎ መረባ እያሉ በመተባበር ነው የምናስታርቀው” ይላሉ፡፡ ‘በደል የደረሰባቸው’ ወገኖችም ከሀገር ባሕል፣ ከዘወልድ ሽማግሌ ማፈንገጥ ስለማይችሉ በተደጋጋሚ ጥረት ለሽምግልና ይስማማሉ ብለዋል፡፡
👉 የዘወልድ ሽምግልና እና የእርቅ ሂደት
በራያ ቤተሰባቸው በሰው የተገደለባቸው ወገኖች በንዴት እና በቁጣ ይሞላሉ፡፡ ቤት እና ትዳራቸውን ይተዋሉ፤ ለበቀል ይነሳሳሉ፡፡ ገዳይም በቀልን ስለሚሰጋ ከነዘመዶቹ ከአካባቢው ሸሽቶ ይቆያል። የገዳይ ወገኖችም ወደ ዘወልድ ሽማግሌዎች ቀርበው ነፍስ ጠፍቶብናልና ነገር አብርዱልን ብለው ያመለክታሉ።
የዘወልድ ሽማግሌዎችም ከቤተሰቦች ጋር ኾነው የሟችን ቀብር ያስፈጽማሉ፤ በተጓዳኝም ችግሮችን እያበረዱ ይቆያሉ። ብዙም ሳይቆይ ለእርቅ ይቀረባል፡፡ የዘወልድ ሽማግሌዎች የሚበይኑትን የደም ካሳ ለማገዝ እንዲሁም በእርቁ አለመገኘት እርቁን እንደመናቅ ስለሚቆጠር የገዳይ ወገን በሙሉ ለእርቅ ይቀርባል፡፡
የአካባቢ ሚሊሻም ታራቂዎች እና የአካባቢውን ሰላም ይቆጣጠራሉ፤ ኅብረተሰቡም በእድር፣ በሚዜ ግንኙነት፣ እርቁ እንዲሳካ ይጥራል።
ግድያው የተፈጸመው በድንገተኛ ግጭት ወይም ታስቦበት መኾኑ ተለይቶ እና ሌሎችም ምክንቶች ግምት ውስጥ ገብተው ገዳይ ለሟች ወገን ካሳ ከፍሎ እና ሌሎች ብያኔዎችንም ለማክበር ተስማምቶ እርቅ ይፈጸማል፡፡ በዚህም ደም መመላለስ ይቆማል፤ መፈናቀል ይቀንሳል፡፡ በዘወልድ የእርቅ ሥርዓት “ችግሩ በተፈጠረ እና ከሀገሬ ወጥቼ በተሰደድኩ በሦስት ወሬ ታርቄ ቤቴ መግባት አስችሎኛል” የሚሉት አቶ እጅጌ “ለዘወልድ ምን ዋጋ እንደሚከፈለው አላውቅም” በማለት ያመሠግናሉ፡፡ ሽማግሌዎቹ በነጻ የሚሰጡትን አገልግሎትም ያደንቃሉ፡፡
👉 ዘወልድ እና ተግዳሮቱ
በ‘ሕግ እና ሳይንስ’ ሽፋን የውጪ ባሕል የተጫነበት ዘወልድ ተግዳሮቶች እያጋጠሙት እንደኾነ ነው የሚነገረው፡፡ ኾኖም ግን አቶ ተመቸ እንደሚሉት የዘወልድ ሽማግሌዎች ያለማንም ተጽዕኖ በጥሩ ሁኔታ ማስታረቃቸውን ቀጥለዋል፡፡ ለማስታረቅ የታሰረን ሰው እስከማስፈታት የሚደርስ ተቀባይነት አላቸውም ባይ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ግን አሁን ላይ ሽማግሌዎቹ ለተለያዩ አካላት ጉዳይ ፈጻሚ ተደርገው እንደሚታዩ ይገልጻሉ፡፡ መሳሪያ የታጠቀ በመብዛቱ ችግሮችን በጉልበት የመፍታት አዝማሚያ መብዛቱም ሌላኛው ተግዳሮት እንደኾነ ይነገራል። የሽምግልና ሥርዓቱ አደረጃጀት እና አሠራር ሕጋዊ ዕውቅና እንዲኖረው የተሠራው ሥራ እምብዛም እንደኾነ ነው ባለሙያዎች የሚናገሩት፡፡
ሥርዓቱ ቃላዊ እንጂ የተጻፈ አለመኾኑ ለወጥነቱ ሌላኛው ተግዳሮት መኾኑን ነው መምህር በላይ የጠቀሱት። በዘወልድ እርቅ ከተፈጸመ በኋላ በሕግ ትፈለጋለህ ብሎ መውሰዱም የዘወልድን ቅቡልነት ያሳንሰዋል የሚልም ስጋት አለ፡፡
👉 ዘወልድን ለማጎልበት ምን መሥራት ያስፈልጋል?
የራስን ችግር በራስ የመፍታትን ባሕላዊ እሴቱን ማኅበረሰቡ አጥብቆ እንዲይዝ ባለሙያዎቹ መክረዋል፡፡ ባሕላዊ እሴቱ እንዲሰነድ፣ ሕጋዊ ዕውቅና እንዲኖረው በማድረግ አደረጃጀት እና አሠራሩን ማጠናከር እንዲሁም ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ ማድረግ ከመንግሥት የሚጠበቁ መኾናቸውም ተመላክቷል፡፡
እነ አቶ ተመቸ ያጋጠማቸው ችግር ‘እድሜ ለዘወልድ’ ታርቀው እና ክሰው አድባር ቀያቸው ላይ በሰላም እየኖሩ ነው፡፡ የዘወልድ ሽማግሌዎች ”አቀበት እና ቁልቁለት ወጥተውና ወርደው ሳይሰለቹ ስላስታረቁን ወደ ሞቀ ቤታችን እንድንገባ አድርገውናል” ሲሉም ያመሠግናሉ፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!