“የሻደይን በዓል በልዩ ድምቀት ለማክበር ተዘጋጅተናል” የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር

0
229

ባሕር ዳር: ነሐሴ 2/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ሻደይ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከነሐሴ 16/2016 ዓ.ም እስከ ነሐሴ 21/2016 ዓ.ም ድረስ የሚከበር የሴቶች ባሕላዊ ጨዋታ ነው። ይህንን በዓልም በደማቅ ሁኔታ ለማክበር ቅድመ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሕል እና ቱሪዝም መምሪያ ተወካይ ኀላፊ ጣምተው ገላስ ገልጸዋል።

“ሻደይ ባሕላችን ለሰላማችን እና ለአንድነታችን” በሚል መሪ መልዕክት ከኹሉም ወረዳዎች በተውጣጡ ልጃገረዶች፣ ታዳጊዎች እና እናቶች በሰቆጣ ከተማ እንደሚከበር ነው የገለጹት፡፡ ለዚህም አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ተወካይ ኀላፊው አስረድተዋል። ሻደይ ሃይማኖታዊ መሠረት ያለው መኾኑን ያወሱት አቶ ጣምተው በዋግ ኽምራ ባሉ ሁሉም ቀበሌዎች፣ አድባራት፣ ወረዳዎች እና ከተማ መሥተዳደሮች በዓሉ እንደሚከበር ነው የተናገሩት።

ባለፉት ሁለት ዓመታት በጸጥታ ምክንያት በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ደረጃ በዓሉ ባይከበርም በዓሉ ሕዝባዊ መሠረት የያዘ በመኾኑ በየአካባቢያቸው አክብረው እንደነበር ነው ያስታወሱት፡፡ ተወካይ ኀላፊው በዚህ ዓመት ግን ካለፉት ዓመታት ለየት ባለ መልኩ በሰቆጣ ከተማ፣ በባሕላዊ ጨዋታ፣ በቁንጅና ውድድር፣ በፓናል ውይይት እና መሰል ትርዒቶች ታጅቦ እንደሚከበር ገልጸዋል።

በአካባቢው ያለው አንጻራዊ ሰላም የተሻለ በመኾኑ የዋግ ተወላጆች፣ ዋግ ኽምራን የሚወዱ እንዲኹም ለጥናት ፍላጎቱ ያላቸው እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ፡- ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here